የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 39 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 39 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 39 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ።
የተቋሙ የፕላኒንግና ቢዝነስ ልማት መምሪያ ዳይሬክተር ብርሃነ ገብረእግዚአብሔር ተቋሙ ባለው ቀጠናዊ ሁኔታ ሳይበገር የአገሪቱን ጭነቶች ሲያጓጉዝ ቆይቷል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ተቋሙ በራሱ አብረውት ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ መርከብ ድርጅቶች ጋር በመሆን 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ቶን በማጓጓዝ የእቅዱን 119 በመቶ መፈፀሙን ገልፀዋል።
በድርጅቱ መርከቦች 266 ቶን በማጓጓዝ የእቅዱን 126 በመቶ መፈፀሙንም ነው ያስረዱት።
ይህንንም ተከትሎ በዘጠኝ ወራቱ 34 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 39 ቢሊየን ብር ማግኘት መቻሉንም አስረድተዋል።
በዚህም ከታክስ በፊት 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ትርፍ ለማግኘት ታቅዶ 6 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
ተቋሙ ወደ አገር የማይገቡ በዓለም አቀፍ ወደቦች ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር የሚጓጓዝ ጭነት ላይ እየሰራ ያለው ተግባር አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ የሚያስችል እንደሆነም ነው ያስረዱት።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የገበያ ማፈላለግ ሥራ በመሥራት 9 ሺህ ቶን ማጓጓዝ መቻሉን ተናግረዋል።