ማህበሩ በአማራ ክልል ከ323 ነጥብ 6 ሚሊዬን ብር በላይ ወጭ የሰብዓዊና የልማት ፕሮጀክቶችን እየተገበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ በአማራ ክልል ከ323 ነጥብ 6 ሚሊዬን ብር በላይ ወጭ የሰብዓዊና የልማት ፕሮጀክቶችን እየተገበረ ነው
ባህር ዳር፣ግንቦት 22/2016 ( ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአማራ ክልል ከ323 ነጥብ 6 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰብዓዊና የልማት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
ማህበሩ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች በባህር ዳር ከተማ ስልጠና እየሰጠ ነው።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሻምበል ዋለ እንደገለጹት፤ ማህበሩ በሰብዓዊ ድጋፍና በልማት ስራዎች ላይ በማተኮር እየሰራ ይገኛል።
ማህበሩ በ2016 በጀት ዓመት ከ323 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ በመመደብ ከ73 ሺህ በላይ አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የድንገተኛ ጤና አገልግሎት፣ የንጽህናና ውሃ አቅርቦት፣ የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም የአምቡላንስ፣ የመድኃኒትና ሌሎች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዬን በላይ ቋሚ አባላት እንዳሉት ጠቁመው ሚዲያዎችና የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎችም ከማህበሩ ጋር በቅንጅት የመስራት ልምዳቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል ።
በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የኮሙኒኬሽን ዲፓርትመንት ሃላፊ አቶ ዘውዱ አያሌው በበኩላቸው፤ ኮሚቴው በዓለም ላይ በ192 ሀገራት በተቋቋሙ የቀይ መስቀል ማህበራት አማካኝነት ተግባራቱን እያከናወነ ይገኛል።
"የሰብዓዊ ድጋፍና የተጎጂዎችን ጥበቃ ስራውን እያከናወነ የሚገኘው በገለልተኝነት፣ ከአድሎ በፀዳ መልኩና በነጻነት እንዲሁም በጎፈቃደኝነትንና ዓለም አቀፋዊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው" ሲሉ አስታውቀዋል።