የኮንስትራክሽን ዘርፉ በመሠረተ ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው - አቶ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ውስጥ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በመሠረተ ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ 2024" የተሰኘ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አውደ ርዕይና ሲምፖዚየም በሚሊኒየም አዳራሽ ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።

"ኢትዮጵያን እንገንባ" በሚል መሪ ኃሳብ በሚካሄደው አውደ ርዕይ መክፈቻ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እና ሌሎች ሚኒስትሮችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በመሠረተ ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ያለው ድርሻ 21 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል።

በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ መሠረት የመንገድ፣ የባቡር፣ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ግንባታ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው፤ መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግና ኢንቨስስመንትን ለመሳብ አበረታች ምህዳር እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉ በየዓመቱ ከ8 በመቶ በላይ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም የሀገርን ብልፅግና ለማሳካት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የቅንጅት ስራ ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

80 በመቶ የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማቅረብ የሚያስችል አቅም መኖሩንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ አኳያ አውደ ርዕዩ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችን ከዓለም አቀፍ ቋማትና ጋር በማስተዋወቅ፣ ትስስር በመፍጠር ልምድ እንዲቀስሙ ያስችላል ነው ያሉት።

ከዛሬ ግንቦት 22-24/2016 ዓ.ም የሚካሄደውን አውደ ርዕይ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአጋር አካላት ጋር አዘጋጅተውታል።

ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው በዚህ አውደ ርዕይ፥ የኢትዮጵያ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የተርክዬ፣ የቻይና፣ የሕንድ፣ የሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ የእንግሊዝ፣ የአልጄሪያ፣ የኦማንና የኳታርን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ከ150 በላይ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ይቀርባሉ።

ከዚህ ውስጥ 41ዱ አገር በቀል ናቸው ተብሏል።

በምህንድስና፣ በፕሮጀክት አስተዳደር፣ በቴክኖሎጂ፣ በመሠረተ ልማትና በሕንፃ ግንባታ ዙሪያ ተከታታይ ሙያዊ የጎንዮሽ የፓናል ውይይቶች ይደረጋሉ።

አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለፈጠራና ለኢንቨስትመንት ምቹ እድል የሚፈጥር ነው ተብሏል።

ከግንባታ ማዘመን እስከ አገልግሎት ያለውን ሂደት በማሳደግ ስማርት ሲቲን ለመገንባት የሚያስችል ልምድና ዕውቀት የሚገኝበት ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም እንደሆነም ተገልጿል።

ከአውደ-ርዕዩ ጎን ለጎን በዘርፉ ያሉ የዕድገት ዕድሎች፣ የከተማ ንድፍ፣ ግንባታ፣ የፕሮጀክት አመራር፣ ኪነ-ህንፃና መሠረተ ልማት፣ ዘላቂ ልማትና ቴክኖሎጂ ላይ ውይይቶች ይደረጋሉ።

የመጀመሪያው ቢግ 5 ኮንስትራክሽን ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ በርካታ ኩባንያዎች በተገኙበት ግንቦት/2015 ዓ.ም መካሄዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም