የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታ ልዩና ታሪካዊ እድል ይዞ የመጣ ነው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታ ልዩና ታሪካዊ እድል ይዞ የመጣ መሆኑን በአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች ገለጹ። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፉን ትናንት ማስጀመሩ ይታወቃል። 

በሂደቱ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ግብአታቸውን የሚያዘጋጁበትና በአገራዊ ጉባኤው የሚወክሏቸውን ተሳታፊዎች የሚመርጡበት ነው።

በምክክሩ ላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው ከየወረዳው የተመረጡ ተወካዮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የማህበራት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ከሶስቱ የመንግስት አካላት የተወጣጡ የተቋማት ተወካዮችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በምክክር ሂደቱ ከንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወይዘሮ ማርታ ሁንዴ እና አቶ ግርማ ሙላት፤ የምክክሩ ጉዳይ የዘላቂ ሰላምና የሀገር ህልውና ጠንካራ መሰረት የሚቀመጥበት መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሀገራዊ ምክክር ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታ ልዩና ታሪካዊ እድል ይዞ የመጣ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁላችንም በባለቤትነት ለመስራት ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ሌላኛው የንግዱ ማህበረሰብ ተወካይ አቶ ሙዘሚል ጀማል እና ወይዘሮ ማርታ፤ ምክክሩ ይዞ የመጣውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ደረጃ የተጀመረው ምክክር ምዕራፍ እስከ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን በተመሳሳይ ሌሎች አካባቢዎችም ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ከቅድመ ዝግጅት በመነሳት፣ የዝግጅት ምዕራፉን በማጠናቀቅ ወደ ምክክር ምእራፍ የገባ ሲሆን በቀጣይነትም ወደ የትግበራ ምዕራፍ የሚገባ ይሆናል። 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም