የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የወጭና ገቢ ንግድን በማሳለጥ ለሀገሪቷ የምጣኔ ሃብት እድገት ያለውን የላቀ ሚና አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የወጭና ገቢ ንግድን በማሳለጥ ለሀገሪቷ የምጣኔ ሃብት እድገት የሚያደርገውን የላቀ ሚና አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በህዝብ ተወካቶች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ  ቋሚ ኮሚቴ  አሳሰበ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዋና መስሪያ ቤት የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝቷል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር ከሚገኙት 27 የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል የብዙዎቹ አፈፃፀም በጥሩ ስኬት ላይ ይገኛል።

ከእነዚህ መካከል ደግሞ የሀገሪቱን 94 በመቶ የገቢና ወጪ ንግድ የሚያሳልጠው የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አንዱና ተጠቃሽ ተቋም ነው።

በዚህ ረገድ የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በዋና መስሪያ ቤቱ በመገኘት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የተቋሙ ሰራተኞችና ኃላፊዎችም ጋር ውይይት አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ኢንጅነር ስለሺ ኮሬ (ዶ/ር)፤ ድርጅቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የአሰራር ስርአት በመከተል የወጭና ገቢ ንግድን ለማሳለጥ የጀመረውን ጥረት አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስን ታላቅ ሀገራዊ ሃላፊነት በመረዳት የተቋሙ ሃላፊዎችና ሰራተኞች በጥሩ መናበብ የሚያከናውኗቸውን የተለያዩ ተግባራትም በተግባር መረዳት ችለናል ብለዋል።

በመሆኑም የዓለም የባሕር ትራንስፖርት አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት በዚህ ወቅት አገልግሎቱን ሳያቋርጥ በትጋትና በስኬት መቀጠሉን አድንቀዋል።

የዚህም ስኬት የተቋሙ ሃላፊዎች፣ አጠቃላይ ሰራተኞችና ባለሙያዎች የተቀናጀ ጥረት ውጤት መሆኑን ጠቅሰው በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል። 

በተለይም የኦፕሬሽን ስራ የሚመራባቸው እና ደንበኞች የሚስተናገዱባቸው መምሪያዎች፣ የድርጅቱን የኦፕሬሽን ስራዎች መከታተያ ክፍል (Situation room) እና ዘመናዊ ዳታ ሴንተር ሊደገፉና ሊበረታቱ የሚገባቸው ስራዎች ናቸው ብለዋል። 

ለድርጅቱ ቀጣይነት ያለው ስኬት ደግሞ የቋሚ ኮሚቴው እገዛ ድጋፍና ክትትል በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ፤ ለወጭና ገቢ ንግድ መሳለጥ የሀገሪቷ ቁልፍ ተቋም በመሆኑ በዚሁ ልክ በዘመናዊ አሰራሮች ታግዞ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ  ወንድሙ ደንቡ፤  ቋሚ ኮሚቴው ላደረገው ምልከታና ለሰጠው ግብአት ምስጋና አቅርበዋል።

በቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ የተነሱ ጉዳዮችን መሰነቅና የተሻለ ተግባራትን ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠው በቀጣይ ትኩረት ይሻሉ በተባሉትም ላይ ይበልጥ እንተጋለን ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሞጆ ወደብና ተርሚናል ግንቦት 03 ቀን 2016 ዓ.ም. ተመሳሳይ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም