የህብረተሰብ ተወካዮች በአጀንዳ ሃሳቦች ላይ እያደረጉት ያለው ውይይት እንደቀጠለ ነው

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ እያስተባበረ የሚገኘው የምክክር ምዕራፍ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ 

ከትላንት ከሰአት ጀምሮ በነበረው መርሃ-ግብር ተሳታፊዎች በየህብረተሰብ ክፍላቸው በቡድን በመሆን ከወከሉት ማህበረሰብ በአደራ ያመጧቸውን የአጀንዳ ሀሳቦች ላይ ውይይት እያደረጉ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

በሂደቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የኛ የሚሉትን እና የተስማሙባቸውን የአጀንዳ ሀሳቦች በማጠናከር ለኮሚሽኑ በቃለ-ጉባኤ ተፈራርመው ያቀርባሉ፡፡

እነዚህ የአጀንዳ ሀሳቦችም በቀጣዩቹ ቀናት በሚኖሩ መድረኮች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ይንፀባረቃሉ፡፡ 


 

ዛሬ ከሰዓት በሚኖረው መርሃ-ግብርም ተሰብሳቢዎች በቀጣዮቹ የምክክር ምዕራፎች ላይ የሚወክሏቸውን 121 ተወካዮች በመምረጥ ለሚቀጥሉት የምክክር ምዕራፎች ይዘጋጃሉ፡፡ 

ኮሚሽኑ እያስተባበረ የሚቆየው ይህ የምክክር ምዕራፍ በቀጣዮቹ ቀናት ተጨማሪ የአራት ባለድርሻ አካላት ተወካዮችን በማሳተፍ እየተከናወነ  እንደሚቀጥል ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም