ቀጥታ፡

ባንኩ ይፋ ያደረገው መተግበሪያ ዳያስፖራው ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ ይበልጥ እንዲያጠናክር ምቹ ዕድል የሚፈጥር ነው - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፋ ያደረገው መተግበሪያ ዳያስፖራው ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ ይበልጥ እንዲያጠናክር ምቹ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለገደብ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ያደረገ ሲሆን መተግበሪያው በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በቀጥታ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ተብሏል። 

(Itsmydam.com) የተሰኘው መተግበሪያ ተሻሽሎ የተዘጋጀ ሲሆን በዚህም ኢትዮጵያውያን ገንዘብ በማዋጣት ድጋፍ የሚያደርጉበት ስርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

መተግበሪያው ኢትዮ-ዳይሬክት ከተሰኘው መተግበሪያ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ በውጭ የሚገኙ ዜጎች መሳተፍ እንዲችሉ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ወቅት፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ የበኩላቸውን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያበለጸገው መተግበሪያ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴ ግድቡ የሚደርጉትን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ምቹ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ባንኩ ለግድቡ ግንባታ መሳካት ጉልህ ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል።


 

ባንኩ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ካሉበት ሆነው ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መተግበሪያ አበልጽጎ ይፋ ማድረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር "itsmydam" የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርኼ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። 


 

የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዛሬ ይፋ የሆነውን መተግበሪያ ጨምሮ ከዚህ ቀደም በተዘረጉ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስልቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመተግበሪያው በመታገዝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ በዙም ባስተላለፉት መልዕክት በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሀገር ኩራት ለሆነው ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡


 

በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ በበኩላቸው ለህዳሴ ግድቡ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያውያን እንደቀደመው ጊዜ ግድቡ እስኪጠናቀቅ የሚደርጉትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም