አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ የዘርፉን እድገት ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ የዘርፉን እድገት ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የዘርፉን እድገት ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
ሚኒስቴሩ የአምራች ኢንዱስትሪ ማነቆዎችን በመለየት የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ ከግሉ ዘርፍ ጋር ምክክር አድርጓል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የብድር አቅርቦት፣ የግብዓትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም የመሰረተ-ልማትና የገበያ ትስስር በበቂ ሁኔታ አለመኖር የአምራች ኢንዱስትሪው ዋነኛ ማነቆዎች መሆናቸውን በመለየት እየተሰራ ነው።
የባለድርሻ አካላት ቅንጅት አለመኖር የዘርፉ ማነቆ መሆኑ በመለየቱ መፍትሄ ለማምጣት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህን ተከትሎ አምራች ኢንዱስትሪው እስከ 2015 ዓ.ም በአጠቃላይ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ 6 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ እንደነበር አመላክተዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የአሥር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ በማሳደግ ዋነኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ አማራጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተከናወኑ ተግባራት ማምረት አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን በድጋሚ ወደ ስራ መመለስ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ንቅናቄው በዘርፉ የሚስተዋሉ ዋነኛ ማነቆዎችን በመቅረፍ አበረታች ለውጥ እያስመዘገበ ስለመሆኑም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት፡፡
ዜጎች የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ የመፍጠርና የመንግሥት ተቋማት የግዥ መዳረሻቸውን የሀገር ውስጥ ምርት ላይ እንዲያደርጉ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ዘርፉን በተለየ ትኩረት ለመምራት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ብቻ የተመለከተ ፌዴሬሽን ለማቋቋም ሥራ መጀመሩንና የግሉ ዘርፍም እንደ ሀገር ያሉ ዕድሎችን አሟጦ መጠቀም እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ስኳርና ጣፋጭ አምራች ማኅበር አቶ ካሳሁን ገብረጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ አንስቶ ከዚህ በፊት የነበሩ ተግዳሮቶች ተቀርፈው በርካታ አነቃቂ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከጋራጅ ዘርፍ ማኅበር የተወከሉት አቶ ይልማ ለማ በበኩላቸው ከዚህ በፊት አቅማቸው የተዳከመ ማህበራት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመታገዝ መፍታት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
የጭቶ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ስምዖን ሰርጹ መንግሥት የዘርፉን ችግር ለይቶ እየወሰዳቸው ያሉ የማሻሻያ እርምጃዎች ተቋማት የራሳቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ማስቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት የብድር አቅርቦት፣ የግብዓት እጥረት፣ የገበያ ትስስርና የመሠረተ-ልማት ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ካለው ጥረት ባሻገር ዘርፉ ራሱን የቻለ ፌዴሬሽን እንዲኖረው ለማድረግ የጀመረው ጥረት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት አመላካች መሆኑን ባለሃብቶቹ ተናግረዋል፡፡