የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የከፍተኛ ባለስልጣናት ምርጫ ሂደት በይፋ ተጀመረ 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የከፍተኛ ባለስልጣናት ምርጫ ሂደት በይፋ መጀመሩን የአፍሪካ ሕብረት አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ከምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እንደሚመረጥ አመልክቷል።

ምርጫው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በየካቲት ወር 2025 በሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ እንደሚከናወን ሕብረቱ ለኢዜአ በላከው የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል። 

በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበርና ምክትል ሊቀ መንበር እንዲሁም በኮሚሽኑ ስር ያሉ የስድስት ኮሚሽነሮች ምርጫ እንደሚካሄድ ገልጿል።

በምርጫው ላይ የሚሳተፉ እጩዎች የተሳትፎ ፍላጎት መግለጫቸውን ለሕብረቱ የሚያስገቡት በየቀጣናው በተሰጠው የእጩነት ኮታ መሰረት መሆኑንም ኮሚሽኑ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

ምርጫው የሚካሄደው በቀጣናዎቹ መካከል ጊዜ ጠብቆ በሚቀያየረው የእጩ ማቅረቢያ መርሕ አማካኝነት እንደሆነ ነው ሕብረቱ ያስታወቀው።  

ማዕከላዊ፣ምስራቅ፣ደቡብ፣ምዕራብና ሰሜን እጩ የሚቀርብባቸው የምርጫ ቀጣናዎች ናቸው።

በዚሁ መሰረት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ለአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ወንድና ሴት እጩዎችን እንዲሁም የሰሜን ቀጣና ለኮሚሽኑ ምክትል ሊቀ መንበር ወንድና ሴት እጩዎችን ያቀርባሉ።

የማዕከላዊ፣፣ደቡብና ምዕራብ ቀጣናዎች ለስድስቱ ኮሚሽነሮች ምርጫ ለእያንዳንዱ ቦታ በትንሹ አንድ ወንድና አንድ ሴት እጩ ማቅረብ ይችላሉ።

. የግብርና፣ገጠር ልማት፣ “ብሉ ኢኮኖሚ “ እና ዘላቂ ከባቢ አየር፤

. የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ኢንዱስትሪና ማዕድን፤

. የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን፤

. የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ፤

. የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት፤

 . የጤና፣ ሰብአዊ ጉዳዮችና ማህበራዊ ልማት፤  ስድስቱ የኮሚሽነሮች ምርጫ የሚካሄድባቸው የስልጣን   ቦታዎች ናቸው። 

እያንዳንዱ ቀጣና እጩዎችን የሚመርጥበት የራሱ አሰራር መዘርጋት የሚችል ሲሆን፤ ቀጣናዎቹ የሚያቀርቧቸው እጩዎች ብቻ ተቀባይነት እንደሚኖራቸው ነው ሕብረቱ ያስታወቀው።

"Panel of Eminent Africans" የተሰኘ ከአምስቱ ቀጣናዎች የተወጣጣ አምስት አባላት ያሉት ቡድን የእጩዎች የተገቢነት ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮችን እንደሚያጣራ ጠቁሟል። 

ኢትዮጵያዊቷ አንጋፋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ ደግሞ የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና በመወከል የቡድኑ አባል ናቸው፡፡

በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀብ የተጣለባቸው አባል አገራት እጩ ማቅረብ እንደማይችሉ ተገልጿል።

እጩዎችን የማቅረቢያ ጊዜ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይም ተጠቁሟል።

በምርጫው ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ እጩዎች የትምህርት ማስረጃቸውን የአፍሪካን የለውጥ አጀንዳ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚችሉና አህጉሪቷ እያገጠሟት ያሉ የቆዩና አዳዲስ ፈተናዎችን በምን መልኩ ለመፍታት እንዳሰቡ ከሚያሳይ የራዕይ መግለጫ ሰነድ ጋር እንዲያቀርቡ ሕብረቱ አሳስቧል።

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባደረገው 22ኛ ልዩ ስብስባው በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የከፍተኛ አመራሮች ምርጫ ዝግጅት ላይ ውይይት ማድረጉ የሚታወስ ነው። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም