የልማት ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ከመከታተል ባሻገር ዲጂታል የግዥ ስርዓትን በማጠናከር የሙስና ተጋላጭነትን መቅረፍ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ የልማት ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ከመከታተል ባሻገር ዲጂታል የግዥ ስርዓትን በማጠናከር የሙስና ተጋላጭነትን መቅረፍ እንደሚገባ የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።    

ፌዴራል የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ዙሪያ ያደረገውን የስጋት ትንተና ጥናት በሚመለከት ከሚኒስቴሩና ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው በዚሁ ጊዜ ፤በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ስር ያሉ ስነ ምግባር መከታተል ክፍሎች የተጠናከረ አደረጃጀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

ይህም የጸረ ሙስና ትግሉን ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርገው ነው የገለጹት፡፡

በተለይ የመንግስት የግዥ ስርዓትን በዲጂታል አሰራር በማጠናከር ለሙስና እና ብልሹ አሰራር በር ሊከፍቱ የሚችሉ ጉዳዮችን ማስወገድ እንደሚገባ በጥናቱ መመላከቱንም ነው ያነሱት፡፡

የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ክትትልና ቁጥጥር ዙሪያ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ መሰል ችግሮችን በማስተካከል ዙሪያ ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡

የስነምግባር መከታተያ ክፍሎችን በሚገባ ማጠናከር እና አፈፃፀማቸውን በመገምገም የተደራጀ የጸረ ሙስና ትግል እንዲኖር መስራት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)  በበኩላቸው የተቋማቱን አሰራር ዲጂታል በማድረግ ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ይህም ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመቅረፍ ምቹ እድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ በጥናቱ የተቀመጡ ምክረ ሃሳቦችን ገቢራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር)፤ የኮሚሽኑ የስጋት ተጋላጭነት ጥናት ውጤታማ የጸረ ሙስና ትግል ለማከናወን አንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡


 

በቀጣይም ጥናቱን መሰረት በማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም