በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በትብብር ይሰራል

ዲላ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በትብብር እንደሚሰራ ገለጸ።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ የግብርና ልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።


 

የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ታምራት አሰፋ በዚሁ ወቅት፤ በመስክ ምልከታው የአካባቢው የልማት ስራዎች ያሉበትን ሁኔታ ማየታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በጌዴኦ ዞን እየተከናወኑ ያሉት የኩታ ገጠም ግብርና እንዲሁም የቡና ልማት ስራዎች በበጎ መልኩ የሚታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትብብር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) በዞኑ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በዞኑ ልማት ላይ በጎ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም በዞኑ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ውጤት እንዲያመጣ እያገዘ እንደሆነ ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው በክልሉ ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓትና ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ይጠናከራል።

በቀጣይም የክልሉ መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ በመስራት የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ መፋጠን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

በመስክ ምልከታ በክልሉ የሚገኙ ከ18 በላይ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም