የቤተ ክርስቲያን ዋናው ፈተና ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚመጣ ነው - ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ የቤተ ክርስቲያን ዋናው ፈተና ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚመጣ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ-ጉባዔ ዛሬ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በጉባዔው መክፈቻ ባስተላለፋት መልዕክት፤ ቤተክርስቲያን በአሁኑ ግዜ በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈች መሆኑን ጠቅሰው በተለይም በውስጧ የሚነሱ ፈተናዎች ተልዕኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ እንቅፋት ሆነውባታል ብለዋል።

በተለይም በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የሚስተዋለው የገንዘብና የሥልጣን ፍቅር እያየለ መለያየትና መነቃቀፍ እየሰፋ መምጣቱን ነው የተናገሩት።  

በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ከኦርቶዶክሳዊ ቀኖናና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ ራስን በራስ የመሾም አባዜ እየተለመደ መምጣቱንም ጠቅሰዋል። 

ይህም ብቻ ሳይሆን ሃይማኖትና ባህልን የማይወክሉ ኃይለ-ቃላት ኃላፊነት በጎደለው አገላለጽ እየተሰነዘሩ "በጎቻችንን አስበርግገዋል" ሲሉም ገልፀዋል። 

ድርጊቱ የቤተክርስቲያኗን የሃይማኖት አባቶች በምዕመኑ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነትና ተደማጭነት አደጋ ውስጥ እየከተተው መሆኑንም አስገንዝበዋል። 

እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመወያየትና ሕግን መሠረት በማድረግ መፍታት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ እርስ በርስ መወቃቀስ እንደማይገባም ነው ያሳሰቡት። 

በተለይም በስፋትና በጥልቀት በመወያየት ሁሉንም ሊያስማማ በሚችል መልኩ ወደ ሰላምና ዕርቅ ሊያደርስ የሚችል ሥራ መሥራት እንሚገባ ተናግረዋል። 

በደልን በካሳና በዕርቅ በይቅርታና በምህረት በመዝጋት ተመሳሳይ በደል እንዳይፈጸም አስተማማኝ የሆነ ተቋማዊ ሥርዓት ማበጀት እንደሚገባም ገልፀዋል።  

አሁን ላይ በአገሪቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት እንደሚገባ ገልጸው፤ ለሀገር ሕልውናና ደኅንነት የሚበጅ ነገር እንዲመጣ ቤተክርስቲያን የበኩሏን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚገባት ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር ዛሬ የተጀመረው ርክበ ካህናት ወሳኝና ወቅታዊ እንዲሁም ሐዋርያዊና ቀኖናዊ በሆኑ የቤተክርስቲያኗ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለቤተክርስቲያንና ለሀገር የሚበጁ ነገሮችን በማየት ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ አሳስበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም