በሀገራችን ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ላይ በእርጋታና በስክነት በመምከር የመፍትሔው አካል ለመሆን ተዘጋጅተናል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ በሀገራችን ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ላይ በእርጋታና በስክነት በመምከር የመፍትሔው አካል ለመሆን ተዘጋጅተናል ሲሉ በአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊ ወጣቶች ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከሚገኙ 119 ወረዳዎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል፡፡

ከምክክር ምዕራፉ ተሳታፊ ወጣቶች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች፤ በሀገራችን ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ላይ በእርጋታና በስክነት በመምከር የመፍትሔው አካል ለመሆን ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የግጭትና ጦርነት አዙሪት አብቅቶ የቆየ ታሪኳ፣ ክብርና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እንዲዘልቅ በተለይም ወጣቶች ድርብ ኃላፊነት አለብን ሲል ወጣት አስማማው መኮንን ተናግሯል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ መሠረት ኑርዬ፤ ምክክሩን በትልቅ ጉጉት ስትጠብቀው የነበረ መሆኑን የሀገራችን ዘርፈ-ብዙ ችግሮች መፍትሔ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ተዘጋጅተናል ብላለች።

ለሀገር የሚጠቅሙ ነገሮችን ሁሉ ወጣቱ አስተዋጽዖ ሊያበረክት ይገባል ያለው ደግሞ ወጣት ዮሐንስ ማስረሻ ነው።

ሌላኛዋ የምክክር ምዕራፉ ተሳታፊ እልፍነሽ አባቡ፤ በተለያዩ ምዕራፎች በስኬታማ ሂደት ላይ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ለችግሮቻችን የጋራ መፍትሔ ለማምጣት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በመሆኑ ተደስተናል ብላለች። 

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ከምክክር የተሻለ አማራጭ ስለሌለ በተለይም ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እናደርጋለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም