ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ወደ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መሸጋገሩ ትልቅ ተስፋና ደስታ የሰነቀ ሆኗል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ወደ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መሸጋገሩ በሁላችንም ዘንድ ትልቅ ተስፋና ደስታ የሰነቀ ሆኗል ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ተናገሩ። 

በአዲስ አበባ ከሚገኙ 119 ወረዳዎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል፡፡


 

ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደቱ የቅድመ ዝግጅትና የዝግጅት ምዕራፉን በስኬት አጠናቆ በዛሬው እለት የምክክር ሂደቱን የጀመረ ሲሆን፤ በዚህ ሂደትም የአጀንዳ ግብአት የሚያዘጋጅበትና በሀገራዊ ጉባዔ የሚወከሉ ተሳታፊዎች የሚመርጡበት ይሆናል። 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ስለመሆኑ ገልፀዋል። 

ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መሸጋገሩ በሁላችንም ዘንድ ትልቅ ተስፋና ደስታ የሰነቀ ሆኗል ሲሉም ተናግረዋል።

በታሪክ አጋጣሚዎች ለዘመናት ያስተናገድናቸውን ዘርፈ-ብዙ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሁነኛ መፍትሔ ሊሆን የሚችል ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ይዞት የመጣውን ወርቃማ ዕድል በመጠቀም ለሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመሻት መዘጋጀት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ የምክክር ሂደቱ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልፀዋል። 


 

የምክክር ሂደቱ አካታች፣ ግልጽና ተዓማኒነት በመከባበር ላይ ተመስርቶ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በአዲስ አበባ በተጀመረው የምክክር ምዕራፍ ከ2 ሺህ 500 በላይ ተወካዮች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች በምክክርና በውይይት የአጀንዳ ሀሳቦችን ማምጣት፣ አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግና በማደራጀት የመፍትሔ ሃሳቦችንም የሚያንሸራሽሩ ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም