የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚያደርጉበት መተግበሪያ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መተግበሪያ ይፋ አድርጓል። 

"itismydam" የተሰኘው መተግበሪያ ይፋ የማድርጊያ መርኃ-ግብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መስሪያ ቤት እየተካሄደ ሲሆን የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በዚህ ወቅት  ባንኩ ለግድቡ ግንባታ መሳካት ጉልህ ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል።


 

ባንኩ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ካሉበት ሆነው ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መተግበሪያ አበልጽጎ ይፋ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በዚህም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር  "itsmydam" የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል።

መተግበሪያው ዓለምአቀፍ ተደራሽነት ያለው፣ ለአጠቃቀም ቀላል እና አስተማማኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመተግበሪያው አማካኝነት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርኼ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። 

የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስም ዛሬ ይፋ በሆነው መተግበሪያና ከዚህ ቀደም በተዘረጉ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስልቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም