የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ብክለትና የውሃ ብክነትን መከላከል የሚችል ቴክኖሎጂ እያበለፀገ ነው

ጂንካ ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ብክለትና የውሃ ብክነትን መከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ እያበለፀገ መሆኑን ገለጸ።

የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች እና የአመራር አባላት በዩኒቨርሲቲው የበለጸገውንና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በማከምና በማጥራት ለግብርና አገልግሎቶች ለማዋል የሚያስችል ቴክኖሎጂን ጎብኝተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉዲሼ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ቴክኖሎጂው የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።


 

ቴክኖሎጂው በቀን እስከ 300 ሜትር ኪዩብ የማጣራትና የተጣራ ውሃን የማከም አቅም ያለው ሲሆን ከአምስት ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት ያስችላል ብለዋል።

ቴክኖሎጂው የውሃ ብክነትን እና የአከባቢ ብክለትን የመከላከል አቅም ያለውና የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ሚዛን በጠበቀ መልኩ የሚሰራ ነው ያሉት።

ግንባታው ከተጀመረ ስድስት ወራት ያስቆጠረው ፕሮጀክቱ የማስፋፊያና የመስመር ዝርጋታዎችን ጨምሮ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለታልም ብለዋል።

አሁን ላይ ፕሮጀክቱ በከፊል አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ሁለት ዓመታት ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ነው ያሉት።

በቀጣይም በቴክኖሎጂው ላይ ተግባር ተኮር ስልጠና በመስጠት በስፋት በማበልፀግ የቴክኖሎጂ ሽግግር ይደረጋል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዓለሙ አይላቴ በበኩላቸው ቴክኖሎጂው የአፈር ለምነትን የሚጠብቁ የአፈር ማዳበሪያዎችን የማምረት አቅም አለው ብለዋል።

ይህም ዩኒቨርሲቲው ለሚያከናውነው የተቀናጀ የግብርና ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

ጂንካ ዩኒቨርሲቲ  አካባቢ ብክለትና የውሃ ብክነትን መከላከል ከሚችል ቴክኖሎጂ በተጨማሪ  በምርምር ያላመዳቸውን የተሻሻሉ የእንስሳትና የሰብል ዝርያዎችን ዛሬ አስጎብኝቷል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም