በምክክርና በሃሳብ ልእልና ችግሮችን መፍታት መቻል ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሀገራዊ መፍትሄ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ በምክክርና በሃሳብ ልእልና ችግሮችን መፍታት መቻል ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሀገራዊ መፍትሄ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከሚገኙ 119 ወረዳዎች የተወጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል፡፡


 

የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ወደ ሶስተኛው ምዕራፍ መሸጋገሩን በይፋ አብስረዋል።

በዛሬው እለት የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ በቀጣይ ለሚከናወነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና የሚኖረው መሆኑንም አንስተዋል።

በአዲስ መንገድ በምክክር ችግሮችን መፍታት የግድ ስለመሆኑ ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ስር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮችን በስክነት በመመካከር መፍታት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል። 

በምክክርና በሃሳብ ልእልና ችግሮችን መፍታት መቻል ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሀገራዊ መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰው ተወካዮችም ለዚሁ ስኬት አሻራችሁን የምታሳርፉበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

በታማኝነት፣ አካታችነትና በግልጽነት ተወካዮች ትርጉም ያለው ተሳትፎ የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰው ለዚህም ኮሚሽኑ ሃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በእስካሁኑ ሂደቱ የቅድመ ዝግጅትና የዝግጅት ምእራፉን በስኬት አጠናቆ በዛሬው እለት የምክክር ሂደቱን ጀምሯል።

በመጨረሻም የትግበራ ምእራፉን በማከናወን በኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ የሚያደርግ ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም