በክልሉ የፈጠራ ስራዎችን  በመደገፍ ከዘርፉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ 

ሆሳዕና ፤  ግንቦት 21 ቀን 2016 (ኢዜአ) ፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን በመደገፍና በማጠናከር ከዘርፉ  የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ ።

"አዲስ አስተሳሰብ ለዲጅታል ለውጥ" በሚል መሪ ሀሳብ በሀዲያ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን መምሪያ የተዘጋጀ  የምርምርና ፈጠራ ስራዎች  አውደ ርዕይ በሆሳዕና ከተማ ተከፍቷል።

የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በወቅቱ እንዳሉት፤ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን መደገፍ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎትና ምርታማነት ለማጎልበት እድል ይፈጥራል።

በክልሉ ይህንን በማጠናከር ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን በመደገፍና በማብቃት  ከዘርፉ  የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ለዚህም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች እንዲበራከቱ በግብአትና በሰው ሀይል እንዲሁም በስልጠናና መሰረተ ልማት ተደራሽነት የመደገፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ በበኩላቸው ፤ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለህብረተሰቡ  ማዳረስ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

ለዚህም ስኬት የዞኑ አስተዳደር የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶችን በመደገፍና በማብቃት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በግልና በቡድን የሚሰሩ አበረታች የሆኑ የፈጠራ ስራዎች መኖራቸውን የተናገሩት ደግሞ የሀዲያ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን መምሪያ ሃላፊ  አቶ ታምራት አኑሎ ናቸው ።

የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎቹን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትና በመደገፍ ለስኬት እንዲበቁ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን  አስረድተዋል።

የአውደ ርዕዩ ዓላማም የፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበው ይበልጥ እንዲጎለብቱ ለማስቻል፣ ተሞክሮን ለማስፋፋትና  መነሳሳትን ለመፍጠር   መሆኑን ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው  አውደ ርዕይ ላይ  የተለያየ የፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም