የምክክር ሂደቱ  መልካም እድሎችን ከማምጣት  ባለፈ  ለአፍሪካውያን  ተምሳሌት  የምንሆንበት  ነው -ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ አገራዊ  የምክክር ሂደቱ  መልካም እድሎችን ከማምጣት ባለፈ  ለአፍሪካውያን  ተምሳሌት  የምንሆንበት  ወቅት ላይ  መድረሳችንን ያሳያል  ሲሉ  የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተናገሩ  ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን መድረኩን በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት በቀጣዮቹ ቀናት የምናከናውነው አጀንዳ የማሰባሰብ  ተግባር  እጅግ መሰረታዊ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮችን አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ  በመለየት  በምክክር ችግሮችን  ለመፍታት መሰረት ይጥላል   ብለዋል።

ለዚህም የማህበረሰብ መሪዎች፣ሴቶች፣ወጣቶች መምህራን የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም እድሮች  ተሳትፏቸውን የሚያበረክቱበት  እድል ማመቻቸቱን  ገልጸዋል።

 ማንኛውም ችግር የሚፈታው በሀሳብ ልእልና በመሆኑ   ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በመምከር   ሀላፊነታችንን በመወጣት ለሀገራዊ ምክክሩ የበለጠ እንስራም   ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ህዝቡ በተወካዮቹ አማካኝነት ትርጉም ያለው ተሳትፎ በማድረግ ስር የሰደዱ ችግሮችን ከመለየት ጀምሮ በሂደቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እኩል የሚሳተፉበትና አሻራቸውን የሚያሳርፉበት ታሪካዊ መድረክ መፍጠሩንም  አብራርተዋል።

አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ላይም በአዲስ አበባ ከሚገኙ 119 ወረዳዎች የተውጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም