የኢትዮጵያ  የቴክኒክና ሙያ አመራሮች ካውንስል ተመሠረተ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ  የቴክኒክና ሙያ አመራሮች ካውንስል ተመሠረተ።

በዚሁ ወቅት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለሀገራዊ ልማት በመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

ተቋማቱ የክህሎትና የዕውቀት ሽግግር በማድረግ ተልዕኮአቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተመሳሳይ ተልዕኮ ካላቸው ተቀማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተደራጀ መልኩ ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ዘርፉን ለማስተሳሰር የሚያስችል የቴክኒክና ሙያ አመራሮች ካውንስል "ብቁ መሪነት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት'' በሚል መሪ ሃሳብ  በይፋ መመስረቱን ገልጸዋል፡፡


 

ካውንስሉ ተቋማቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጡ እንዲሁም ስራቸውን ተናበው የሚሰሩበት ወጥ የሆነ የአደረጃጀት ስርዓት ለመገንባት የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የአመራር ካውንስሉ ጥናትና ምርምር በማድረግ ልዩነት መፍጠር የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት  ይጠበቅበታል ብለዋል።

ካውንስሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ገበያ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ከማፍራት አንጻር ከምንጊዜውም በላይ ፍጥነትን፣ ፈጠራን ፤ጥራትንና ብዛትን ማዕከል አድርጎ እንዲሰራ አሳስበዋል።


 

የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ከድር በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከ 2 ሺህ በላይ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በመንግሥትና በግል ባለቤትነት ስራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከእነዚህም መካከል ከ100 በላይ  የሚሆኑት  የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ኮሌጆቹ የበርካታ ወጣቶችን ክህሎት በማበልጸግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ስራ እያከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

የበለጸገ ክህሎት የማስጨበጥ ስራው በተለይ ወጣቶች ከራሳቸው ባለፈ ለሀገራቸው ኢኮኖሚ የማይተካ ሚና እንዲጫወቱ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም