ቦርዱ ከማዕከላዊ ሸዋ የኮማንድ ፖስት አመራሮች እና ከሰሜን ሸዋ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላት ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አመራሮችና ከሰሜን ሸዋ ዞን የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሄዱ።

በአካባቢው የሚታየው አሁናዊ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ፣ በሰላም መደፍረስ ሂደት የተያዙ ተጠርጣሪዎች አያያዝና መረጃ አጣርቶ ለፍርድ የማቅረብ እንዲሁም የሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታን በተመለከተ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

በአካባቢው ማንኛውም አካል ያለውን ፍላጎትና ልዩነት ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ተነጋግሮ በመፍታት፤ ለሕብረተሰቡ ዘላቂ የሆነ ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባ የቦርዱ አባላት ገልፀዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች መረጃቸውን የማጣራት ስራ ተካሂዶ እንደየ ወንጀሉ ክብደትና ቅለት ከተሃድሶ ስልጠና እስከ ፍርድ ቤት የማቅረብ ስራ እንደተሰራ እና እየተሰራ እንዳለም የዞኑ ኃላፊዎች ለቦርዱ አባላት ገለጻ አድርገዋል።

በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ የተለያዩ መደበኛ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በኮማንድ ፖስት ስር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ዘላቂ የሆነ ሰላምና ፀጥታን ከማረጋገጥ አኳያ ከአካባቢው የሕብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ወጣቶችን አደራጅቶ ስልጠና እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም