ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት የምንችለው ተቀራርቦ በመነጋገርና ለመፍትሄው በጋራ በመስራት ብቻ ነው-ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ - ኢዜአ አማርኛ
ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት የምንችለው ተቀራርቦ በመነጋገርና ለመፍትሄው በጋራ በመስራት ብቻ ነው-ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 21/2016 (ኢዜአ)፦ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት የምንችለው ተቀራርቦ በመነጋገርና ለመፍትሄው በጋራ በመስራት ብቻ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተናገሩ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል፡፡
አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ላይም በአዲስ አበባ ከሚገኙ 119 ወረዳዎች የተወጣጡ የማህበረስብ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ወደ ሶስተኛው ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል፡፡
በዚህም እኛ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ተቀራርበን ችግሮቻችንን በመፍታት ለበርካታ አገራት አብነት የምንሆንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት የምንችለው ተቀራርቦ በመነጋገር እና ለመፍትሄው በጋራ በመስራት ብቻ መሆኑን በመገንዘብ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
ይህም መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ባህልና ቅቡልነት ያለው አገረ መንግስት ለመገንባት ሚናው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ህዝቡ በምክክር ሂደቱ ትርጉም ያለው ተሳትፎ በማድረግ አሻራውን ማሳረፍ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡