በማዕከላዊ ጎንደር ዞን  በክረምቱ  የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት  እየተከናወኑ ነው

ጎንደር፤ ግንቦት 21/ 2016 (ኢዜአ)፡-  በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጣና ሀይቅ ገባር ወንዞች በክረምቱ   የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ እንዳያደርሱ  ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ  የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

 የጎርፍ መከላከሉ ተግባራት እየተከናወኑ የሚገኙት  የሃይቁ አዋሳኝ በሆኑት ምስራቅ፣  ምዕራብ ደንቢያ እና  ጎንደር ዙሪያ ወረዳዎች መሆኑን የመምሪያው ሃላፊ አቶ ኑረዲን ሰይድ ለኢዜአ  ተናግረዋል።


 

ድርማና አርኖ የሚባሉት የጣና ሀይቅ ገባር ወንዞች በክረምቱ ወራት በውሃ እየሞሉ  አቅጣጫቸውን በመሳት በሰው ህይወት፣ ንብረትና ሰብል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የጎርፍ መከላከል ስራ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰው፤ በዘንድሮ ክረምትም የጎርፍ አደጋን ለመከላከል  የሚያስችሉ ተግባራት 12 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በሁለቱ ወንዞች ግራና ቀኝ 7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጎርፍ መከላከያ የአፈር ግድብ ስራ እየተከናወነ ሲሆን፤ በመጪው ሰኔ ወር  ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በማሽነሪዎች ታግዞ የሚከናወነው የአፈር ግድብ ስራ 95 ሄክታር በሚሸፍን የእርሻ መሬት እና ከ3 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን በወንዙ ሙላት ሳቢያ ሊደርስ ከሚችል አደጋ ለመከላከል እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡


 

የጣና ሀይቅ ገባር የሆነው የአርኖ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላትና አቅጣጨውን በመሳት በሰብልና በቤት እንስሳት ላይ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን ያስታወሱት ደግሞ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር በላይ መኮንን ናቸው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በወንዙ ግራና ቀኝ የተሰራው የአፈር ግድብ ከጎርፍ አደጋ ስጋት እንደታደጋቸው ጠቅሰው፤ ዘንድሮም  የጎርፍ መከላከያ ግድቡ ስራው ቀጥሎ እንዳለ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

በክረምት ወቅት የድርማ ወንዝ በሚፈጥረው የውሃ ሙላት በተደጋጋሚ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ  በምስራቅ ደንቢያ ወረዳ የሮቢት ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጀምበሩ ሙሉአለም ናቸው፡፡

በወንዙ ግራና ቀኝ የተሰራው የአፈር ግድብ ከጎርፍ አደጋ እየታደጋቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ዘንድሮም ተጨማሪ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ያለው ስራም ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጣና ገባር ወንዞችን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎች በክረምት ወቅት ሊደርስ የሚችልውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም