በአዲስ አበባ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 21/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ ይጀመራል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መርሃ ግብር የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮች ወደ ተዘጋጀው ቦታ እየተሰባሰቡ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው የምክክር ምዕራፍ ከ2 ሺህ 500 በላይ ተወካዮች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

በምክክር ምዕራፍ መርሃ ግብሩ ሶስት ዋና ዋና ተግባራት የሚከናወኑ ሲሆን እነሱም ተሳታፊዎች በምክክርና በውይይት የአጀንዳ ሀሳቦችን ማምጣት፣ አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ ያሰባስባሉ፣ ያደራጃሉ እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳቦችን ያንሸራሽራሉ፡፡


 

በመጨረሻም የሂደቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ፡፡

በመርሐ ግብሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተሳታፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የመንግስት አካላትና የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች ይመካከራሉ፡፡

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአሥር ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች በክልላዊ የምክክር ምዕራፍ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን ከየኅብረተሰብ ክፍሉ ማስመረጡ ይታወሳል፡፡

ኮሚሽኑ በቀጣይነት ተመሳሳይ መርሃ-ግብሮችን በክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ያከናውናል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በ2014 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ ከቅድመ ዝግጅት በመጀመር የዝግጅት ምእራፉን በስኬት አጠናቋል።


 

በመቀጠልም በዛሬው እለት የምክክር ሂደቱን የሚጀምር ሲሆን በቀጣይነትም በትግበራ ምእራፉ ስራውን የሚያጠናቀቅ ይሆናል።

በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ የሚጀመረው ሶስተኛው ምዕራፍ የምክክር ሂደት ሲሆን ለምክክሩ ውጤታማነት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

አለመግባባትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የውይይት ባህልን ማዳበር ከተቋቋመበት አላማ ውስጥ ይጠቀሳል።

የምክክር ሂደቱን በአካታችነት፣ በግልጽነት፣ አሳታፊነትና በተአማኒነት የሚካሄድ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም