በክልሉ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስቀጠል ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር የሚሰሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ 

ሀዋሳ ፤ግንቦት 20/2016 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል የተጀመረውን ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማስቀጠል ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር የሚሰሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

"በትብብርና ፉክክር ሚዛን ላይ የተመሰረተ ውይይት ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከርዕሰ መስተዳድሩ ጋር በሀዋሳ ከተማ ተወያይተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በአገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ላይ መድረስና በትብብር መስራት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው።

በክልሉ እየተከናወነ ያለው የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው በምክክርና ትብብር የዳበረ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት መገንባት እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

ለእዚህም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ በትብብር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

መድረኩም የዴሞክራሲ ስነምህዳር መስፋት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ በፓርቲዎቹ የሚነሱ ሀሳቦች የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለመሙላት ስለሚያግዙ ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

የአገር ግንባታ ስራውን በትብብርና በመተጋገዝ ስሜት ማከናወን ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጉዞ ማሳካት እንደሚቻልም አቶ ደስታ ገልጸዋል።

የልማት ግቦችን ለማሳካት ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከመንግስት ጋር ተቀራርበው በትብብር መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ምርታማነትን ማሳደግና ገበያውን ማረጋጋት የክልሉ መንግስት ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም  የልማት ግቦች ተቀርፀው እየተተገበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።። 

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ የሰላምና ልማት ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው እድል መፈጠሩን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ናቸው።


 

በክልሉ የተቋቋመው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፓርቲዎቹ በክልላዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው እንዲሰሩ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

የዴሞክራሲ ምህዳሩን የሚያሰፉ መሰል መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው፤ በመድረኩ በፓርቲዎች የሚነሱ ሀሳቦች ግብዓት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ በለጠ ሲጌቦ በበኩላቸው፤ "ክልሉ ካለው የልማት አቅም አንጻር ብዙ መስራት ስለሚጠበቅ የህዝባችን ኑሮ ለማሻሻል በትብብር እንሰራለን" ብለዋል።

የሰላምና ጸጥታ ስራው በቴክኖሎጂ መደገፉ ሰላምን ለማጠናከር ፋይዳው የላቀ በመሆኑ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።

በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆናቸው አጠናክሮ ለማስቀጠል በትብብር እንሰራለን ያሉት ደግሞ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ተወካይ አቶ ገዛኸኝ አርጊሶ ናቸው።

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው መመልከታቸውንና ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። 

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ሊቀመንበር አቶ ለገሰ ላንቃሞ በበኩላቸው በክልሉ ህዝብን የሚጠቅሙ የልማት ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ከመንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በተለይ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በትብብር እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም