የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና አብሮነት ለማጠናከር ለግጭት መንስኤዎች  መፍትሄ በመፈለግ  ኃላፊነታችንን እንወጣለን 

 ሚዛን አማን፤ ግንቦት 20/2016 (ኢዜአ)፦  የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና አብሮነት ለማጠናከር ለግጭት መንስኤዎች  መፍትሄ በመፈለግ  ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል  የብሔረሰቦች ምክር ቤት አባላት ገለጹ ።

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት በሰላም ግንባታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በቴፒ ከተማ አካሂዷል።

ከክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አባላት መካከል ወ/ሮ አረጋሽ አዘዘው በወቅቱ እንደገለፁት፤ የግጭት መንስኤዎችን ለይቶ መፍትሄ መፈለግ ለሰላም ግንባታ  ቀዳሚ ተግባር በመሆኑ ለአካባቢያቸው ሰላም መቀጠል የበኩላቸውን እየተወጡ ነው።

የምክር ቤቱ አባል አቶ አገኘሁ ወርቁ፤ ''የክልሉን ሰላም ለማስቀጠል ከወከለን ሕዝብ ጋር በቅርበት በመወያየት ተግባብቶና ተቻችሎ የመኖርና የመሥራት ተሞክሮንና ባህልን የማስፋት ተግባር እያከናወንን እንገኛለን'' ብለዋል።

ሰላምን ዘላቂ ማድረግ የሚቻለው የግጭት ምንጮችን በንግግር መፍታት ሲቻል በመሆኑ ለተግባራዊነቱም   ግንዛቤ የመፍጠር ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ከበደ ቡርጂ በበኩላቸው፤ የመከባበር፣ የመቻቻል እና ችግሮችን ተነጋግሮ በሽምግልና ሥርዓት የመፍታት ባህልን በማጎልበት ለዘላቂ ሰላም መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ የሰላም እሴቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በቅንጅት የመሥራት ልምድን ለማሳደግ የድርሻቸውን እንሚወጡም ገልጸዋል።

የሕዝቦችን ጥቅም  ለማስጠበቅ   የድጋፍና ክትትል ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን  የገለፁት ደግሞ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኩ ናቸው።

የብሔረሰቦችን እኩልነት እና ልማት ለማረጋገጥ ምክር ቤቱ ቅድሚያ ለሰላም   መስጠቱን  አረጋግጠዋል።

በተለይም በክልሉ ያሉ ቱባ የሆኑ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ዕሴቶች ጎልተው በመውጣት ልማትን እንዲያግዙ ምክር ቤቱ በተቀናጀ መንገድ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣም አብራርተዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ የምክር ቤት አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም