ቀጥታ፡

የፓኪስታን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሳተፍ ይሻሉ

 አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎች በመጠቀም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው የፓኪስታን ባለኃብቶች ገለጹ።

 የፓኪስታን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ልዑክ በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማየትና የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ለማድረግ ግንቦት 18/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።

ልዑካን ቡድኑ ትላንት በተካሄደው የኢትዮ-ፓኪስታን የቢዝነስ ምክክር መድረክ ከኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

ኢትዮጵያ የተሟላ መሰረተ ልማት፣ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭና ምቹ የአሰራር ምህዳር እንዳላት ለባለኃብቶቹ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለኃብቶችም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለኢንቨስትመንት ምቹ አገር መሆኗን እንደተመለከቱ ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ያላት ምቹ የአየር ጸባይ፣ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የገነባቸው መሰረተ ልማቶችና ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያለው የወጣት ሰው ኃይል ባለቤት መሆኗን ትኩረታቸውን እንደሳበው ጠቁመዋል።  

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጭ ባለኃብቶች የሚያቀርበው የኢንቨስትመንት ማበረታቻና እድል በመጠቀም በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሠማራት ፍላጎት እንዳላቸው ነው የፓኪስታን ባለኃብቶች የተናገሩት። 

የፎርዋርድ ግሩፕ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካሃዋጃ ማሶድ፤ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ተግባራዊ ያደረገችው ፖሊሲ የሚያሰራ ነው ብለዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን ኢንቨስትመንት ለማካሄድ የሚያስችሉ የኢንዱስትሩ ፓርኮችን ጨምሮ መሰረተ ልማቶችንና ሌሎች ምቹ አካባቢዎች መኖሩንም ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የአየር ጸባይና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት የሰው ኃይል በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር የገለጹት ደግሞ የኤር ሲአል ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፋዜል ጂላኒ ናቸው።  

 

የኢትዮ-ፓኪስታን የንግድ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ኢብራሂም ካሊድ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያና ፓኪስታን አሁን ላይ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገር እየሰሩ ነው ብለዋል። 


 

ሁለቱ አገራት በቀጣይ በኢንቨስትመንትና ንግድ ዘርፎች ባሉት አማራጮች ላይ በመሥራት ያላቸውን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያብራሩት። 

ከ80 በላይ የፓኪስታን ከፍተኛ ኢንቨስተሮችን ያካተተው የልዑካን ቡድን የአዳማ፣ የቦሌ ለሚና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሥራ እንቅስቃሴንና አጠቃላይ የምርት ሂደትን ጎብኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም