ኢትዮጵያ በአእምሯዊ ንብረት፣ በጄኔቲክ ሃብት እና ተዛማጅ ማህበረሰባዊ እውቀት ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈረመች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአእምሯዊ ንብረት፣ በጄኔቲክ ሃብት እና ተዛማጅ ማህበረሰባዊ እውቀት ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈረመች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአእምሯዊ ንብረት፣ በጄኔቲክ ሃብት እና ተዛማጅ ማህበረሰባዊ እውቀት ታሪካዊ ነው የተባለውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈርማለች።
የዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት አባል ሀገራት በአእምሯዊ ንብረት፣ በጄኔቲክ ሃብት እና ተዛማጅ ማህበረሰባዊ እውቀት ላይ አዲስ ታሪካዊ ስምምነትን አጽድቀዋል።
የዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት (WIPO) አባል ሀገራት እ.ኤ.አ ከግንቦት 13 እስከ 24/2024 በጀኔቭ ባካሄዱት ዲፕሎማቲክ ኮንፍረንስ ስምምነቱ መጽደቁን የአእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ስምምነቱ በጄኔቲክ ሃብት እና በተዛማጅ ማህበረሰባዊ እውቀት ላይ ተመስርተው ለሚቀርቡ የፓተንት ማመልከቻዎች አመልካቾቹ የፈጠራዎቻቸውን የዘረመል ሀብቶች እና ተዛማጅ ማህበረሰባዊ እውቀቶች መገኛ ምንጭ እንዲገልጹ የሚያስገድድ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም የፓተንት ሥርዓቱን ውጤታማነት ፣ ግልጽነት እና ጥራትን ለማሳደግ እንደሚረዳና በዘረመል ሀብቶች እና ተያያዥ ባህላዊ እውቀት ላይ አዲስነት ወይም ፈጠራዊ ብቃት የሌላቸው ፈጠራዎች ያለአግባብ ዕውቅና እንዳያገኙ ለመከላከልም ያስችላል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያን በመወከል የመጨረሻውን ሰነድ የፈረሙት የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመሰል ኢትዮጵያ ስምምነቱን ስትፈርም የዘረመል ሀብቶችን እና ተያያዥ ባህላዊና ማህበረሰባዊ እውቀቶችን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በኃላፊነት እና በፍትሃዊነት ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ቀጣይ ሁኔታ በመገንዘብና በማለም ነው ብለዋል፡፡
አባል ሀገራት የጋራ ቅርሶቻቸውን ለማክበር እና ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት ስምምነቱ ይወክላል ፤ ይህም ለትውልድ የእውቀት እና የብልጽግና ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል ሲሉ አክለዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት መፈጸሟ ያላትን የበለፀገ የዘረመል ሀብቷን እና ባህላዊ እውቀቷን በመጠቀም፣ ሁሉም ማህበረሰቦች ላበረከቱት አስተዋፅኦ ተገቢውን እውቅና እና ጥበቃ እንዲያገኙ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አያይዘው አብራርተዋል።
ስምምቱን እውን ለማድረግ በአለም የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ መሪነት ላለፉት 23 ዓመታት የተለያዩ ድርድሮች ሲደረጉ መቆየቱም ተገልጿል።