ቀጥታ፡

ከተጋነነ የካሳ ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ፕሮጀክቶች እየተስተጓጎሉ ነው - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል  

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ባሉባቸው አካባቢዎች ከተጋነነ የካሳ ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ በክርክር፣ በቅሬታና በአቤቱታ ላይ መሆኑን ገለጸ። 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፍና ማከፋፈል የሚያስችሉ ግንባታዎችን እያካሄደ ነው። 

ተቋሙ በአዋጅ ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል የኃይል ማመንጫ ግንባታ ዋነኛው ሲሆን  ከውኃ፣ ከንፋስ፣ ከደረቅ ቆሻሻና ከከርሰ ምድር እንፋሎት (ጂኦተርማል) የኃይል አማራጮች የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል።

ይሁን እንጂ ተቋሙ ግንባታ በሚያከናውንባቸው አካባቢዎች የካሳ ክፍያና ተያያዥ ጉዳዮች  ፕሮጀክቶችን በጊዜ ለማጠናቀቅ እንቅፋት እንደፈጠረባቸውና ተቋሙ የበጀት ጫና ውስጥ እንዲገባ እያደረገ መሆኑን የተቋሙ የሕግ ክፍል ዳይሬክተር መርክነህ ይገዙ ገልጸዋል።

ኃላፊው ይህን ያሉት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ላይ ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1161/2011 ማሻሻያ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው።

በውይይቱ ንብረት ገማች አካላት ሥራቸውን በባለቤትነት መንፈስ ባለመውሰድ ንብረቶቹ ከሚያወጡት ዋጋ በላይ የተጋነነ ግምት እንደሚሰጡም ተገልጿል።

የካሳ ክፍያ ገማች አካላት ልማቱ ለየአካባቢው የሚያመጣውን ዘላቂ ጥቅም ከማሰብ ይልቅ ግለሰቦችና ቡድኖች ባልተገባ መንገድ እንዲጠቀሙ እንደሚያደርጉ በጥናት ጭምር መረጋገጡም ተጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕግ ክፍል ዳይሬክተር መርክነህ ይገዙ፤ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ባሉባቸው አካባቢዎች ከተጋነነ የካሳ ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች እያጋጠሟቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

በተለይም በገማቾች የሥነ-ምግባር ችግር የተጋነነ የካሳ ክፍያ እየተጠየቀ መሆኑን ገልጸዋል። 

  የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ ኃይል በአሁኑ ወቅት ከ340 ሚሊዮን ብር በላይ ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ በፍርድ ቤት እንደታገደበት አብራርተዋል።

በፍርድ ቤት ከታገደው ገንዘብ በተጫማሪ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ በክርክር፣ በቅሬታና በአቤቱታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

ይህም በተለያዩ አካባቢዎች የሚሰሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዳይውሉ ማድረጉን አንስተዋል።

የፌዴራል ተቋማትን የመሰረተ ልማት ግንባታ የካሳ ክፍያ የፌዴራል መንግሥት የሚሸፍን መሆኑን ባልተገባ መንገድ በመረዳት የሚከናወኑ ያልተገባ የካሳ ክፍያ ግመታና ሌሎችም ገፊ ምክንያቶች አዋጁን ለማሻሻል መነሻ መሆናቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበረው ውይይት ተጠቁሟል።

የሚሻሻለው አዋጅም እነዚህን ችግሮች በማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት  ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የሚሻሻለው ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ የፌዴራል መንግስቱ በሚያከናውናቸው የመሰረተ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ግንባታዎች ላይ የተጋነነ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎችን ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።

በአዋጁ ማሻሻያ እንደተመላከተው፣ የፌዴራል መንግሥት ለሚያከናውናቸው የልማትና የማኅበራዊ አገልግሎት ማስፋፊያ ግንባታዎች ንብረት የመገመት የመክፈልና የማስነሳት ሥራ ሙሉ ለሙሉ ለክልልና ከተማ አስተዳደሮች ተሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም