ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የሀይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም የተከናወኑ አመርቂ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የሀይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም የተከናወኑ አመርቂ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፦ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የሀይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም የተከናወኑ አመርቂ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
በመዲናዋ የኮሪደር ልማት ስራ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የተቀናጀ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
በአዲስ አበባ በመከናወን ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ግንባታው በመፋጠን ላይ ይገኛል፡፡
ይህንን ተከትሎ በመዲናዋ የሚሰሩ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተናበበ መልኩ እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማት አዲስ የስራ ባህልን በማስተዋወቅ ለኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት መልካም እድል አስገኝቶለታል፡፡
በመዲናዋ ከኮሪደር ልማቱ ጎን ለጎን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዳይቋረጥ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ደንበኞች የሃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥማቸው ጊዜያዊ መፍትሄ በመስጠትና ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ ስራዎቹ በፍጥነትና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
በኮሪደር ልማት ምክንያት ወደሌላ አካባቢ የተዘዋወሩ ዜጎች በአጭር ጊዜ ኤሌትሪክ እንዲያገኙ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
አገልግሎቱ ከ2010ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ በአራት ምዕራፍ የተከፈለ የኤሌክቲሪክ አገልግሎት የዲስትሪቢዩሽን ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ የተቋሙ መረጃዎች ያሳያሉ።
አሁን ላይ በሁለት ምዕራፍ የተሰሩት ስራዎች መጠናቀቃቸውንና የሶስተኛው ምዕራፍ አፈፃፀም 73 በመቶ መድረሱ አራተኛው ምዕራፍ ደግሞ በ2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ መረጃዎች አመላክተዋል።