ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የቴክኖሎጂ እውቀቱ ያደገ የሰው ሀይል ለማፍራት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ደሴ፣ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የቴክኖሎጂ እውቀቱ ያደገ የሰው ሀይል ለማፍራት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የዲጂታላይዜሽን ፕሮግራም የአቅም ግንባታ የስልጠና መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ስቡህ ገበያው እንደገለፁት፤ ዘመኑን የዋጀ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ሀይል መገንባት ያስፈልጋል።

ለዚህም በቴክኖሎጂ በመታገዝ ብቃት ያለውና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ በሚገኙ 126 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በአጫጭርና ረጃጅም ስልጠናዎች ክህሎትና ተግባር ተኮር ስልጠና በመስጠት ብቁ ዜጋ እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በውጭ ሃገር ስልጠና ጭምር ተወዳዳሪ የሰው ኃይል እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የተጀመረው ሁለተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል።

ዛሬ የተጀመረው የዲጂታላይዜሽን ስልጠናም ለተከታታይ አራት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን ኋላቀር አሰራሮችን በመቅረፍ የሪፖርት አደራረግ ዘዴዎችን ለማሻሻል የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።

እንዲሁም ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ለመለየት፣ ጊዜን፣ ጉልበትንና ወጪን ለመቀነስ እንደሚረዳ ገልፀው ቢሮው በዲጅታል ቴክኖሎጂ ቀዳሚ በመሆን የተሻለ ስራ ለማከናወን የሚያደርገውን ጥረትም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ይትባረክ ጌታሁን በበኩላቸው፤ የተጀመረው የቴክኖሎጂ አሰራር ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይልን ለመገንባት ያግዛል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ የስራ እድል ፈጠራ ድግግሞሽ እንዳይኖርና ኢ-ፍትሃዊና ቀጣይነት ያለው የስራ እድልን ለመፍጠርና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ገልፀዋል።

''በከተማው የሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ክህሎት፣ ተግባርና ፍላጎት መር ስልጠና በመስጠት በቁ ዜጋ እንዲፈጥር ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው'' ብለዋል።

''በተለያየ ጊዜ የሚሰጡ ተግባር ተኮር ስልጠናዎች የተሻለ ስራ መስራት እንድንችል እድል ፈጥሯል'' ያለችው ደግሞ የከላላ ወረዳ ስራና ስልጠና ጽህፈት ቤት የስራ እድል ፈጠራ ባለሙያ ወይዘሪት ያለላት ሙሉ ናት።

''ዛሬ የተጀመረው የዲጅታላይዜሽን ስልጠና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ብቁና ተወዳዳሪ እንድንሆን ከማድረጉም ባለፈ የውሸት ሪፖርትና በሃሰተኛ መረጃ ቅጥር ለመፈፀም የሚሞክሩ ህገወጥ ግለሰቦችን አደብ ያስይዛል'' ብላለች።

በስልጠናው የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሰራሩን በሐምሌ ወር ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም