ለአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የገንዘብ እና የአውቶቡስ ድጋፍ ተደረገ

ሶዶ፤ግንቦት 20/2016 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ለአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የአንድ ሚሊዮን ብርና የአውቶቡስ ድጋፍ አደረገ።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2016 ዓ.ም የውድድር ዘመንን በአሸናፊነት አጠናቆ ፕሪሚየር ሊጉን ለተቀላቀለው የአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደርጓል። 

በአቀባበሉ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም የክለቡ ደጋፊዎች ተገኝተዋል።  

በዚሁ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ለቡድኑና ለአባላቱ ያለው አድናቆት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ለክለቡ ማበረታቻ እንዲሆንም የአንድ ሚሊዮን ብር እና የአውቶብስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማበርከቱን ነው የገለጹት።

ስፖርት ለሀገር ልማት፣ ህዝቦችን ለማቀራረብና አንድነት ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው አስታውሰው፣ በክልሉ ያለውን የስፖርት አቅም በአግባቡ ለመጠቀም በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ በበኩላቸው በዞኑ ህዝብ ስም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው የህዝቡን አንድነት በማጠናከር ለክልሉ የስፖርት ዘርፍ እድገት በጋራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ህብረብሔራዊ ወንድማማችነትን ከሚያጠናክሩ ተግባራት አንዱ የስፖርቱ ዘርፍ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ ናቸው።

''የአርባ ምንጭ ከተማ እግር ካስ ቡድን በውድድር ዓመቱ ሽንፈትን ሳያስተናግድ በፅናት ላስመዘገበው አኩሪ ድል ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል'' ሲሉም ለክለቡ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

በአቀባበሉ ላይ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች፣ የክለቡ ደጋፊዎችና የስፖርቱ ቤተሰቡ ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም