የፓኪስታን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ልዑክ የአዳማ፣ ቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎበኘ - ኢዜአ አማርኛ
የፓኪስታን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ልዑክ የአዳማ፣ ቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎበኘ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፦ከ80 በላይ የፓኪስታን ከፍተኛ ኢንቨስተሮችን ያካተተው ልዑካን ቡድን የአዳማ፣ የቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
የፓኪስታን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ልዑክ በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማየትና የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ለማድረግ ግንቦት 18/2016 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።
ልዑካን ቡድኑ ትላንት በተካሄደው የኢትዮ-ፓኪስታን የቢዝነስ ምክክር መድረክ ከኢትዮጵያ መንግስት አመራሮች ጋር ተወያይቷል።
ኢትዮጵያ የተሟላ መሰረተ ልማት፣ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ እና ምቹ የአሰራር ምህዳር እንዳላት ለባለሀብቶቹ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
የፓኪስታን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድን በዛሬው ዕለትም የአዳማ፣ ቂሊንጦና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የስራ እንቅስቃሴ እና ያላቸውን መሰረተ ልማት ጎብኝቷል።
በቀጣይ በየዘርፎቹ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመለየት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ የሚያደርጓቸውን ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያና ፓኪስታን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በተለይም በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እየሰሩ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 ዓመታት በኋላ ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ፓኪስታን የንግድና ኢንዱስትሪ ማዕከሏ ካራቺ የጀመረው የቀጥታ በረራ አገልግሎት በሀገራቱ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱ ተገልጿል።