የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሀፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2016(ኢዜአ):- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሀፊ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ ጋር ውይይት አደረጉ።

ሚኒስትሩ እና ረዳት ዋና ፀሀፊው የመንግስታቱ ድርጅት ለሀገራዊ ልማት ዕቅዶች የሚያደርገውን ድጋፍ ማሳደግ በሚያስችሉ ማሻሻያዎች ዙሪያ ሀሳብ መለዋወጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን አጋርነት እና ትብብር የበለጠ በማጠናከር አገራዊ የልማት ጥረቶችን መደገፍ እና ለሰብአዊ ሁኔታዎች ምላሽ መስጠት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም ገንቢ ውይይት ማድረጋቸው ተገልፅዋል።

አገራዊ የትኩረት መስኮችን እና ትልሞችን እውን ለማድረግ ቅንጅትን እና ውጤታማነትን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

አምባሳደር ታዬ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወሳኝ የልማት አጋር እንዲሆን እና ለአባል ሀገራቱ ውጤታማ ድጋፍ ማድረግ እንዲችል የተቋሙን አሰራሮችና ትኩረቶች ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

ሚኒስትሩ አክለውም ዶክተር ራሚዝ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አረጋግጠውላቸዋል።

ዶክተር ራሚዝ በበኩላቸው ጽህፈት ቤታቸው የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም