የአሶሳ ከተማ ስታዲየምን ቀሪ የግንባታ ሥራዎች ለማጠናቀቅ 900 ሚሊዬን ብር በጀት ተመደበ

አሶሳ፣ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፡- የአሶሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታን ለማጠናቀቅ 900 ሚሊዬን ብር በጀት መመደቡን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አህመድ ናስር መታሰቢያ የተሰየመው የአሶሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ የተጀመረው በ2006 ዓ.ም. እንደነበርም ተገልጿል።

ኮሚሽኑ በስታዲየሙ አጠቃላይ የግንባታ ሁኔታ ላይ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካዮች ጋር ዛሬ በአሶሳ ከተማ ውይይት አድርጓል።


 

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ የሱፍ አልበሽር በወቅቱ እንደገለፁት፤ የክልሉ መንግስት የስታዲየሙን ግንባታ ለማስፈጸም ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ ደርሷል።

የስታዲየሙ ግንባታ ክልሉ በጋጠመው የጸጥታ ችግር፣ በበጀት እጥረት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት መዘግየቱን አመልክተዋል፡፡ 

በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ለማጠናቀቅ የታሰበውን የስታዲየም ግንባታ በፊፋ እና በካፍ ደረጃ ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ሶስተኛውና ወሳኝ የሆነውን የግንባታ ምዕራፍ ለማስፈጸም 900 ሚሊዬን ብር መመደቡን ገልጸው በዚህ ዓመት ለሚከናወነው ሥራ ደግሞ የ200 ሚሊዬን ብር በጀት መለቀቁን ጠቁመዋል፡፡


 

የፌደራል መንግስት በተለይም የግንባታ ጥራት ቁጥጥርን ጨምሮ የባለሙያ እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ መወሰኑን አቶ የሱፍ ገልጸዋል፡፡

በሚድሮክ ኮንስትራክሽን የአሶሳ ስታዲየም ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ አባተ፤ አሁን የተጀመረው የስታዲየሙ ሶስተኛ ምዕራፍ ግንባታ የመጫወቻ ሜዳ፣ የአትሌቲክስ መሮጫ መም፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች ዝርጋታ እና ሌሎችንም ወሳኝ ስራዎች እንደሚያካትት አብራርተዋል፡፡

የግንባታው ሶስተኛ ምዕራፍ ሲጠናቀቅ ውድድሮችን ለማከናወን እንደሚያስችል የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ የመጫወቻ ሜዳውን የመገንባት ሥራ መጀመሩንና በታቀደው መሰረት በማጠናቀቅ ለማስረከብ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ የሃብከ ብርሃኔ የውይይቱ ዓላማ ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለሀገር የሚገባውን ጥቅም እንዲያበረክት በማሰብ ነው ብለዋል፡፡

የአሶሳ ስታዲየም በወንበር 30 ሺህ ተመልካቾችን በመያዝ ዓለም አቀፍና አህጉር ዓቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ እየተገነባ እንደሚገኝም በወቅቱ ተገልጿል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም