ድሬዳዋን ፅዱና ምቹ ከተማ ለማድረግ የተጀመረውን ተግባር የሚያግዝ የጽዳትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በወረዳ ደረጃ ተጀምሯል

ድሬዳዋ ፤ ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፦የማህበራዊ አገልግሎቶች ጥያቄዎች ለመፍታት ከሚከናወኑ ልማቶች ጎን ለጎን የተሰሩትን ልማቶች በባለቤትነት ጠብቆ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ገለጹ። 

ዛሬ በአስተዳደሩ ወረዳ ሁለት በመሠረተ ልማቶች ላይ እየደረሱ የሚገኙትን ጉዳቶች ለመከላከል ያስችላል የተባለው ህዝባዊ የጽዳትና አካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

አቶ ኢብራሂም በወቅቱ እንዳሉት በመሠረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመከላከል ልማቶቹን በዘላቂነት ጥቅም እንዲሰጡና ፅዱና ውብ አካባቢን ለመፍጠር ያስችላል።

የማህበራዊ አገልግሎቶች ጥያቄዎች ለመፍታት ከሚከናወኑ የማህበራዊ ልማቶች ጎን ለጎን የተሰሩትን ልማቶች በባለቤትነት ጠብቆ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

በተለይም በጎርፍ መውረጃ ዲቾች፣ በጌጠኛ የድንጋይ ንጣፎች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ እየተፈጠሩ የሚገኙ ብክለቶችን እና ጉዳቶችን በዘላቂነት ለመከላከል እንደሚያግዝ ነው የገለፁት።

ንቅናቄው ድሬዳዋን ፅዱና ውብ የስራ እና የመኖሪያ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶችን ውጤታማ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ የታሰበው ለውጥ እንዲመጣም የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የድሬደዋ ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም በበኩላቸው በጥናት ላይ ተመስርቶ በ193 የወረዳው ቅያሶች(ብሎኮች) የሚከናወኑት የአካባቢ ልማቶች ድሬዳዋን ፅዱና ውብ የማድረግ ዘመቻን ውጤታማ እንደሚያደርጉት ገልጸዋል።

በልማቱ ላይ በተለያዩ የጎጥ አደረጃጀቶች የተዋቀሩ ሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም የማህበረሰብ መሪዎችና ነዋሪዎች የሚሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከየአካባቢዎቹ ቆሻሻዎችን በፍጥነት የማስወገድ  ስራ በመስራት ህብረተሰቡ ራሱን ከተላላፊ በሽታዎች እንዲከላከልም ንቅናቄው ያግዛል ነው ያሉት።

ለአንድ ወር የሚካሄደው የአካባቢ ልማት ንቅናቄ የነዋሪውን የልማት ባለቤትነት ከማረጋገጥ በዘለለ  ህብረተሰቡ ልማቶችን በዘላቂነት እንዲያስተዳድር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ የአካባቢ ልማትና ማህብረሰብ ተሳትፎ ኤጀንሲ ኃላፊ ወይዘሮ ረሂማ አወል ናቸው።

በንቅናቄው  በህገ ወጥ መንገድ የተዘጉ መንገዶች ይከፈታሉ፤ በየስፍራው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ይካሄዳል፤ የቆሸሹና የተበላሹ አካባቢዎች ውብና ፅዱ ይሆናሉ ብለዋል።

 

 
  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም