2ኛው የዓለም አቀፍ  የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፦  'ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ' ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም ለሁለተኛ ጊዜ በአዲስ  አበባ ከግንቦት 22-24/2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአጋር አካላት ጋር በመሆን  ያዘጋጁት ሲሆን ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም በመጪው ሐሙስ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከፈታል።

"ኢትዮጵያን እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን በዘርፉ ያሉ የዕድገት ዕድሎች   እንደሚቀርቡም ተገልጿል።

የጀርመን፣ ጣሊያን፣ ተርክዬ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሌሎች አገራት የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች እንደሚሳተፉም ተነግሯል።


 

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንዳሉት፥ ኤግዚቢሽኑ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማስተዋወቅ እና ዘርፉ በአገሪቱ ዕድገት ላይ እያስመዘገበ ያለውን አበርክቶ ለማሳየት ያስችላል።

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን  እድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችሉ ልምዶች የሚቀስሙበት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ የፋይናንስ፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ትብብር የሚፈጠርበት ነው ብለዋል፡፡

ከግንባታ ማዘመን እስከ አገልግሎት ያለውን ሂደት በማሳደግ ስማርት ሲቲን ለመገንባት የሚያስችል ልምድና ዕውቀት የሚገኝበት ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም እንደሚሆንም ገልጸዋል።

በዲዛይን፣ በግንባታ ጥራትና በፕሮጀክት አመራር ዘርፍ የልምድ ልውውጥ ከማድረግ ባለፈ ዘርፉን የሚያሻግሩ አዳዲስ ዕይታዎች ይቀመሩበታል ነው ያሉት።

ሚኒስትሯ አክለውም በኤግዚቢሽኑ፥ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ 156 ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።


 

የዓለም አቀፉ ዲኤምጂ ኢቨንትስ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ቤን ግሪንሽ ኤግዚቢሽኑ በኢትዮጵያ መካሄዱ እያደገ የመጣውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ከማስተዋወቅ ባለፈ ሰፊ የገበያ ዕድል የሚፈጠርበት መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም