ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ አስር ወራት 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፦  በበጀት ዓመቱ አስር ወራት 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሃና አርያስላሴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሃና አርያስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግስት  ኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ  ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በዚህም አዳዲስ ሴክተሮችን፣ የወጪና ገቢ ንግድ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ዝግ የነበሩ ሴክተሮች ለኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ ደግሞ ከተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለውጭ ባለሀብቶች የሚያስተዋውቁ መረሃ-ግብሮችን በማስተዋወቅ ረገድ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በግብርና፣ በማምረቻ፣በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝም፣በጤና እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች ላይ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች የምትሰጠውን ማበረታቻ እያስተዋወቀች ትገኛለች ብለዋል።


 

በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት የፋይናንስ ዘርፉ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ኮሚሽኑ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እቅድ ይዞ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ 10 ወራት 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ  ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ቻይና ፣ ኔዘርላንድ፣ ቱርክ እና  ህንድ ደግሞ በኢትዮጵያ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከሚሳተፉ ዋና ዋና ሀገራት መካከል መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋለ ንዋይ በማውጣት ቀዳሚውን ደረጃ እንደሚይዙም ነው የጠቀሱት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም