ቀጥታ፡

የተርኪዬ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2016(ኢዜአ)፦ የተርኪዬ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጥሪ አቅርበዋል።

አምባሳደሩ ጥሪውን ያቀረቡት በተርኪዬ ኢስታንቡል በተካሄደው የኢትዮ-ተርኪዬ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት እድሎች መኖራቸውን በመጥቀስ ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ በርካታ ዘርፎችን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ማድረጓን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስንትመንት ሆልዲንግ ምክትል ስራ አስፈጻሚ ያስሚን ወሃብረቢ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ፣ ማበረታቻዎች እንዲሁም አዳዲስ ህጎችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።


 

ምክትል ስራ አስፈጻሚዋ አክለውም የተርኪዬ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ ላይ የሁለቱን ሀገራት የንግድ እንቅስቃሴ በሚመለከት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ መንግስቴ ገለጻ ማድረጋቸው ተመላክቷል።

የተርኪዬ የንግድ ምክትል ሚኒስትር ሙስጠፋ ቱዝኩ እና የተርኪዬ የንግድ ማህበረሰብ ማህበር ፕሬዝዳንት መሀመት አስማሽ በኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት እና የንግድ አማራጮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።


 

ኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ ያላት እና የአፍሪካ መዲና በመሆኗ በሀገሪቱ ኢንቨስት ማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በመገንዘብ የተርኪዬ ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

በፎረሙ ላይ ከ300 በላይ የሁለቱ ሀገራት ባለሃብቶች የተሳተፉ ሲሆን ባለሃብቶቹ የቢዝነስ ለቢዝነስ ውይይት አድርገዋል።


 

ፎረሙ አንካራ የሚገኘው የኢፌዴሪ ሚስዮን ከተርኪዬ የንግድ ማህበረሰብ ማህበር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም