ክልሎቹ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ ዝግጅት በማጠናቀቅ ተከላ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆናቸውን ገለጹ

አዳማ ፤ ግንቦት 20/2016 (ኢዜአ)፡- የኦሮሚያና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ ዝግጅት በማጠናቀቅ ተከላ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆናቸውን የየክልሎቹ ግብርና ቢሮ አመራር አባላት ገለፁ።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የችግኝ ዝግጅትና የሚተከልበት መሬት ልየታ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላቸውንና ለደን ልማት የሚውሉ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ሲደረግ እንደነበረም አስታውሰዋል።

በዚህም በተለይ የክረምት ወቅት ቀድሞ በሚገባባቸው የቦረናና ጉጂ ዞኖች እንዲሁም ከፊል ባሌ ዞን ላይ የተከላ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

''በአብዛኛው የክልሉ ዞኖች የተከላ ጉድጓድ ዝግጅት የማጠናቀቅና ችግኞችን ከችግኝ ጣቢያ ወደ መትከያ ቦታዎች የሟጓጓዝ ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንገኛለን'' ብለዋል።

ከመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ የተከላ ስራ በክልል ደረጃ በይፋ ይጀመራል'' ያሉት ምክትል ኃላፊው ''ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራንም ከወዲሁ እያጠናቀቅን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብሮች የተራቆቱና በአፈር መከላት የተጎዱ ቦታዎች ማገገማቸውን የገለጹት አቶ በሪሶ የደረቁ ወንዞችና ሃይቆች እያገገሙ ከመሆኑም ባለፈ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያገዘ መሆኑንም ተናግረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርናና ገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር በበኩላቸው በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብነት፣ ለመኖና ለደን ልማት የሚውሉ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥ ከ55 በመቶ በላይ የሚሆኑት ለፍራፍሬ፣ ለቡና፣ ለቅመማ ቅመምና ለእንስሳት መኖ የሚውሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም 74 ሺህ ሄክታር መሬት ለመሸፈን መታቀዱን የገለጹት አቶ ዑስማን በአብዛኛው የቡና ችግኞች ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ለተከላ መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ በየም ዞን የአረንጓዴ አሻራ የተከላ ፕሮግራም መጀመሩን ጠቅሰው ህብረተሰቡ በነቂስ እንዲሳተፍበት የንቅናቄ ስራ በተከታታይ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም