ደረጃቸውን የጠበቁ የወጣቶች ስብዕና ማዕከላትን በማስፋፋት ወጣቱን ከአደንዛዥ እፆች ተጋላጭነት ለመጠበቅ የቅንጅት ስራ ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ደረጃቸውን የጠበቁ የወጣቶች ስብዕና ማዕከላትን በማስፋፋት ወጣቱን ከአደንዛዥ እፆች ተጋላጭነት ለመጠበቅ የቅንጅት ስራ ሊጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦ደረጃቸውን የጠበቁ የወጣቶች ስብዕና ማዕከላትን በማስፋፋት ወጣቱን ከአደንዛዥ እፆች ተጋላጭነት ለመጠበቅ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚያዚያ እስከ ሚያዚያ ለአንድ ዓመት ያካሄደው የጸረ-አደንዛዥ ዕፆችና አሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችን የመከላከል አገር አቀፍ ንቅናቄ የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ እንዳሉት፥ ወጣቱ ለአደንዛዥ እፅ ሱስ እንዳይጋለጥ አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት አለበት።
የትምህርት ተቋማትም የወጣቱን ስብዕና ለመገንባት የጀመሩትን ስራ እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
ወጣቶች በአደንዛዥ እፅ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ የስብዕና ማዕከላትን ለማስፋፋት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸው፥ ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የብሔራዊ የዜግነት አገልግሎት አዋጅንና መሰል የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ወጣቶች ለአገር ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ወጣቶች ያላቸውን ዕምቅ አቅም በመጠቀም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን አንስተዋል።
ሀገር ተረካቢ እና አምራች ኃይል የሆነውን ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል በስብዕና መገንባት፣ ከአደንዛዥ ዕፅ እና ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት ነው ብለዋል።
መንግስት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ በማቋቋም ወጣቶችን ከአደንዛዥ እፆችና መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች ለመጠበቅ በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በመድረኩ አስተያየት የሰጡ ተሳታፊዎች ለወጣቱ መልካም ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ከማስፋፋት ባለፈ የሱስ ማገገሚያ ማዕከላትም ተደራሽ ሊሆኑ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በሰጡት ምላሽ የወጣቶችን ተጋላጭነት ለመቀነስ አጋላጭ ሁኔታዎችን በመለየት የመከላከል ስራን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ለሱስ የተጋለጡ ዜጎች የሚያገግሙባቸው ማዕከላት በስራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ሆስፒታሎችና ሌሎች የህክምና ተቋማትም አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።