ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ፓኪስታን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና ፓኪስታን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

ኢትዮ-ፓኪስታን ሁለተኛው ምዕራፍ የቢዝነስ ምክክር መድረክ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች፣ የንግድ ልዑካን እና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካራቺ በረራ ከጀመረ በኋላ ፓኪስታንን ከኢትዮጵያም ባለፈ ከአፍሪካ ጋር ያላት የኢኮኖሚ በተለይም የንግድ ግንኙነት እየተጠናከረ መሄዱን ተናግረዋል።

በቀጣይ ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የዲፕሎማሲ ዘርፎች ያላቸው ግንኙነት ይበልጥ በሚጠናከርባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።

የፓኪስታን የንግድ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሞሃመድ ዙቤር ሞቲዋላ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ማድረጓ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በመሆኑም ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ  የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግና ለጋራ ተጠቃሚነት ትሠራለች  ነው ያሉት።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል።


 

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን እየተገበረች መሆኑን ጠቅሰው፥ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምቹ ምህዳር መፈጠሩንም አብራርተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከፓኪስታን የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ፋርማሲቲካልና ሌሎች የካበተ ልምድ ለመውሰድና ለጋራ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ዝግጁ ናት ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጰያና የፓኪስታን የሁለትዮሽና የኢኮኖሚ ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ወደ ፊት እያደገ የሚሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስረዳት በዚህ ዓመት ብቻ በፓኪስታን ስድስት የቢዝነስ ፎረሞች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።


 

በዚህም ከ80 በላይ የፓኪስታን ባለሀብቶችን የያዘ ልዑክ በለውጥ ጉዞ ላይ በምትገኘው ኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ለማድረግ በአዲስ አበባ ምክክርና ጉብኝት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በ2015 ዓ.ም  የኢትዮጵያ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን ወደ ፓኪስታን ተጉዞ የነበረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ባሉት የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በመምከር የተለያዩ የመግባቢያ ስምምነቶች ላይ መደረሱ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም