ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ተመሰረተ

ቦንጋ ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምስረታ ዛሬ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

በምስረታው መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ብሔራዊ ቦርድ አባል ዶክተር አዲሳለም ሙላት እንዳስታወቁት ማህበሩ ከተመሰረተበት 1927 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ሰብዓዊ እና የልማት ተግባራትን አከናውኗል።

አሁን ላይም ማህበሩ ተልዕኮውን ለማሳካት እና መዋቅሩን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመዘርጋት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ዛሬም የደቡብ ምዕራብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መመስረቱን ተናግረዋል። 

የጽህፈት ቤቱ መመሠረት ማህበሩ የሚሰጠውን የሰብዓዊ ተግባራት ለማጠናከርና ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን  አብራርተዋል። 

 ማህበሩ ጽህፈት ቤቱን የማጠናክር ስራ በቅርበት እንደሚሰራ ገልጸው በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ የአስተዳደር አካላት  ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ  አሳስበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ ማህበሩ በክልሉ የተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በደረሱበት ወቅት የሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀረበውን ጥያቄ መሠረት በማድረግ በክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እንዲከፈት መደረጉ ማህበሩ ይበልጥ የሰብአዊ ድጋፍ ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቅሰው በዚህ ረገድ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የካፋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ እና የምስረታ ጉባኤው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ ከበደ፣ ማህበሩ ባለፉት ሶስት ዓመታት በክልሉ በነበሩ ሶስት ቅርንጫፎች አማካኝነት ከ10 ሚሊዬን ብር በላይ የሚገመት የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በክልሉ ውስጥ እስካሁን ከ145 ሺህ በላይ አባላት እና ከ5 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞችን ማፍራት መቻሉን ጠቁመው አዲሱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መቋቋሙም ይህንን አገልግሎት ይበልጥ ለማስፋት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት  አቶ አስራት መኩሪያ፣ በቀጣይ በሁሉም ዞኖች ቅርጫፎችን በመክፈት እና ህብረተሰቡን በማስተባበር ለማህበሩ አላማ መሳካት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

ጽህፈት ቤቱ ተጠናክሮ የታለመለትን አገልግሎት እንዲሰጥ ባለሀብቶች፣ በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች እና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በምስረታ ጉባኤው ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አመራር አባላት፣ ባለሀብቶች እና የተለያዩ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም