የዜጎችን መብትና ክብር በማስጠበቅ በውጭ ሀገራት የሚሰጠው ህጋዊ የሥራ ስምሪት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን መብትና ክብር በማስጠበቅ በውጭ ሀገራት የሚሰጠው ህጋዊ የሥራ ስምሪት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦ የዜጎችን መብትና ክብር በማስጠበቅ በውጭ ሀገራት የሚሰጠው ህጋዊ የሥራ ስምሪት ትርጉም ባለው መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ኢትዮጵያና ኩዌት በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል፤ ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በኢትዮጵያና ኩዌት መካከል ህጋዊ የሥራ ስምሪት ማድረግ የሚያስችል ድርድር ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ህጋዊ የሥራ ስምሪት ስምምነትም ኢትዮጵዊያን በኩዌት ክብርና መብታቸው ተጠብቆ የስራ ዕድል የሚያገኙበት አዲስ የስራ መዳረሻ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ ዕድል ፈጠራ የአሰራር ማሻሻያ ከተደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እንደሆነም አንስተዋል።
በውጭ ሀገራት የሚሰጠው ህጋዊ የሥራ ስምሪትም ለዜጎች የስራ ዕድል ከማመቻቸት ባለፈ የኢትዮጵያ እና የመዳረሻ ሀገራትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ከፍተኛ ትርጉም አለው ብለዋል።
በኢትዮጵያ እና ኩዌት መካከል የተደረገው ህጋዊ የሥራ ስምሪት ስምምነትም የአዲሱ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የለውጥ እሳቤ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
ህጋዊ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት መዳረሻን በማስፋት የኢትዮጵያዊያን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል የሁለትዮሽ ድርድር እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ዜጎቿ የሚሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ለደህንነት እና ጤናቸው ስጋት የማያስከትሉ መሆናቸውን እንዲሁም መድን፣ ደመወዝና ጥቅማጥቅም የሚያስጠብቅ አቋም ይዛ እንደምትደራደር ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና በመዳረሻ ሀገራት ችግሮችን ቀድሞ ማረም የሚያስችል ክትትል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የፈጠረችው ጠንካራ የመደራደር አቅም፥ መንግስት የዜጎቹን ጉዳይ በአንክሮ የሚከታተል መሆኑን የመዳረሻ ሀገራት እንዲገነዘቡ ስለማድረጉም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ናይፍ ሃፕስ አል ኦይታይቢ፤ ኢትዮጵያና ኩዌት ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት እና የህጋዊ የስራ ስምሪት ግንኙነት እንዳላቸው አውስተዋል።
ዛሬ በኢትዮ-ኩዌት መካከል የተፈጸመው ህጋዊ የሥራ ስምሪት ስምምነትም የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማሳደግ ትብብራቸውን የበለጠ እንደሚያሳድግ አብራርተዋል።
በቀጣይም የሀገራቱን ንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር በማስፋት የሀገራቱን ታሪካዊ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ስምምነቱ ወደ ኩዌት የሥራ ስምሪት የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊያን መብትና ጥቅማቸው ተጠብቆ ህጋዊ የስራ ዕድል የሚያገኙበትን የትብብር ሁኔታ ለመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገልጿል።