ኢትዮጵያዊያን የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች በአለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ለመሳተፍ ሞሮኮ ገቡ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦ 40 የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች የልኡካን ቡድን አባላት በአለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ለመሳተፍ ሞሮኮ ገብተዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት በማራካሽ በሚኖራቸው ቆይታ በምርምር ያበለፀጓቸውን የጤናና የኢንቨስትመንት አዋጭ መተግበሪያዎችን ጨምሮ አምስት የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከተለያዩ የአለም ሃገራት ለተውጣጡ ተመራማሪዎችና የቢዝነስ ሰዎች ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዱባይ የንግድ ማዕከል አማካኝነት በሞሮኮ ማራካሽ በተዘጋጀው በዚህ ልዩ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ አፍሪካን ከተቀረው አለም ሊያገናኝ የሚችል አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ይፋ እንደሚደረግበት የልዑካን ቡድኑ አስተባባሪ ፣ የአብርሆት ቤተመፅሐፍት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ውባየሁ ማሞ ገልፀዋል።

ተመራማሪዎቹ ለሁለት ዓመት በአብርሆት ቤተመፅሐፍት ሲሰለጥኑ እንደነበርም ኢንጂነሩ ገልፀዋል።

የቴክኖሎጂ ተመራማሪ የልዑካን ቡድኑ አባላት በከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም በአብርሆት ቤተመፅሐፍት እና በA2SV አስተባባሪነት የሚሳተፉ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም