ሀገር አቀፍ የሰውነት ቅርፅ ስፖርት ውድድር ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦ አራተኛው ሀገር አቀፍ የሰውነት ቅርፅ ስፖርት ውድድር ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት እና ሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከግንቦት 20 እስከ 22/2016 ዓ.ም በሚደረገው በዚህ ውድድር፥ በሁለቱም ፆታዎች እስከ 300 የሚደርሱ ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የውድድሩ አሸናፊዎችም ዓለምአቀፉ የአካል ብቃትና የሰውነት ግንባታ ፌዴሬሽን፤ በግብፅ በሚያዘጋጀው የአፍሪካ የአካል ብቃት ሻምፒዮና ተሳታፊ ይሆናሉ።

የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት እና ሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት መስፍን እሸቴ፤ የተቀዛቀዘውን የሰውነት ቅርፅ ስፖርት ለማነቃቃት ዕድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል።

ስለሆነም በማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ በቁሳቁስ ድጋፍና ለህብረተሰቡ ስለ ስፖርቱ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት እና ሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን የተቋቋመው በ1962 ዓ.ም በወቅቱ አጠራር ወክማ አራት ኪሎ ወጣቶች ስፖርት ቢሮ እንደሆነ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፌዴሬሽኑ እ.አ.አ በ2023 የዓለም አቀፉ የአካል ብቃትና የሰውነት ግንባታ ፌዴሬሽን አባል መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም