ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር መፋጠን የ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ነጋዴዎች መረጃ በዲጂታል ቋት ተደራጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር መፋጠን የ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ነጋዴዎች መረጃ በዲጂታል ቋት ተደራጅቷል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር መፋጠን እስካሁን የ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ነጋዴዎች መረጃ በዲጂታል ቋት መደራጀቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በ2025 ሀገራዊ አቅሞችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል ስትራቴጂ ቀርፃ እየተገበረች ነው።
ስትራቴጂው ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ፣ የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ የግልና የመንግሥትን ዘርፎች በማስተሳሰር የዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞን ለማሳለጥ ከሚተገበርባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የንግዱ መስክ መሆኑን ገልፀዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ የንግዱን ዘርፍ የዲጂታል ሽግግሩ ዋና ባለቤት ለማድረግ ምቹ ምህዳር እየተፈጠረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ለዚህም ለረዥም ዓመታት ሲያገለግል የቆየው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ከሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ጋር ተቃኝቶ መሻሻሉን ተናግረዋል።
የንግዱ ማኅበረሰብ የንግድ ፈቃድ ምዝገባን ጨምሮ 16 አገልግሎቶችን በበይነ-መረብ አማካይነት ባለበት ሆኖ በተቀላጠፈ መልኩ የሚገለገልበት የዲጂታል ቋት ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱን አክለዋል።
ኢትዮጵያም በዲጂታል ጎራ በዓለም ተወዳዳሪና ተጠቃሚ ለመሆን የኢ-ኮሜርስ ረቂቅ ስትራቴጂ ማዘጋጀቷን ጠቅሰው፤ በቅርቡ ጸድቆ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሀገራዊ የዲጂታል ሽግግሩን ለማፋጠን በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት የ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ነጋዴዎችን መረጃ ወደ ዲጂታል ማህደር መመዝገቡን ተናግሯል።
ይህንን ግዙፍ መረጃ ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ በማከማቸትና በመተንተን ለሀገር ጥቅም ለማዋል በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ የተገነቡ የዳታ ማዕከላት ሚና ጉልህ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ፓርኩ በርካታ ወጣቶች ሥራ የሚያገኙበት እና የቢዝነስ ሽግግር አድርገው ኩባንያ የሚፈጥሩበት ማዕከል በመሆኑ ከንግዱ ዘርፍ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው ብለዋል።
የንግዱን ዘርፍ ዲጂታል ሽግግርን ከማፋጠን አኳያ የባለሙያዎችና የኅብረተሰቡን የዲጂታል ክህሎት ማሳደግ ላይ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኔትዎርክ ትስስር መቆራረጥ ሲያጋጥምም ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።