መንግስት ለፈጠራ ስራ የሰጠው ትኩረት ፈጠራን በማስተዋወቅ የአገርን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ዕድል የሚፈጥር ነው - የፈጠራ ባለቤቶች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦መንግስት ለፈጠራ ስራ የሰጠው ትኩረት ፈጠራን በማስተዋወቅ የሀገርን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የፈጠራ ባለቤት መምህራን እና ተማሪዎች ገለጹ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ "በፈጠራ ሥራ የዳበረ ትውልድ ለሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ ከተማ አቀፍ የተማሪዎች የሳይንስና የፈጠራ ውድድር አውደ ርዕይ ማካሄዱ ይታወሳል። 


 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሳይንስና የፈጠራ ውድድር አውደ ርዕይ ተሳታፊ እና የፈጠራ ባለቤት መምህራን እና ተማሪዎች እንደሚሉት ፈጠራ የሀገርን ዕድገትና ብልጽግና ለማሳለጥ የማይተካ ሚና ይጫወታል።

መንግስት ለፈጠራ ስራ የሰጠው ትኩረት ፈጠራን በማስተዋወቅ የሀገርን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም  ተናግረዋል። 

የጂቫ የመጀመሪያ ደረጃ  ትምህርት ቤት ተማሪ ክርስቲና ጳውሎስ መንግስት ለፈጠራ ስራ የሰጠው ትኩረት የፈጠራ ስራዋን እንድታስተዋውቅና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንድታደርግ እድል እንደፈጠረላት ተናግራለች። 

የከተማ ግብርናን  ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መስራቷን በመግለፅ ወደ ተግባር ለመቀየር መዘጋጀቷን ገልፃለች። 

ቴክኖሎጂው ውሃ ቆጣቢና የተፈጥሮ ማዳበሪያን ለማዘጋጀት እንደሚያስችልም ገልጻለች።


 

የአቡነ ባስሊዎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነጋ ፀጋየ የበጋ መስኖ ምርታማነትን ማሳደግ የሚችል በትንሽ ኃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ቴክኖሎጂ  መስራቱን ተናግሯል።

የውሃ መሳቢያው በኤሌክትሪክና በታዳሽ ኃይል የሚሰራ በመሆኑ የአየር ብክለት የማያስከትል የፈጠራ ስራ መሆኑን በመግለፅ ከውጭ የሚገባ ምርት የሚተካ መሆኑንም አስረድቷል። 

በቀጣይ ፈጠራውን ማሳደግ የሚችልበት የገንዘብ ድጋፍ  ከተደረገለት ቀጥታ ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚችል ገልጿል። 


 

የገዳምስታዊያን ማርያም ፅዮን  ካቶሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሃይሉ ካሴ የመማር ማስተማር ስርዓቱ የንድፈ ሀሳብ ትምህርትን ከተግባር ትምህርት ጋር በማቀናጀት እንዲያስተምሩ ዕድል በመፍጠሩ የፈጠራ ባለቤት  የሆነ ትውልድ ማፍራት መቻላቸውን ተናግረዋል። 

ሁሉም የፈጠራ ስራዎች የሀገር ልማትንና እድገትን የሚያፋጥኑ መሆናቸውን ተገንዝቦ መደገፍና ማበረታታት  እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ  መምህር ዘውዱ ዘነበ ናቸው። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም