ከግንቦት 21 ጀምሮ ለሚካሄደው የምክክር ምዕራፍ መሳካት ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ከግንቦት 21 ጀምሮ ለሚካሄደው የምክክር ምዕራፍ መሳካት ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016(ኢዜአ)፦ ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ ም ጀምሮ ለሚካሄደው የምክክር ምዕራፍ መሳካት ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የከተማ አስተዳደር የምክክር ምዕራፉን በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚጀምርም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ፤ ከነገ በስቲያ ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚካሄደውን የምክክር ምዕራፍ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ለምክክር ምዕራፉ አስፈላጊው ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን ለሂደቱ መሳካት ሁሉም የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ ም የሚካሄደው መድረክም ሶስት ዋና ዋና ተግባራት እንደሚከናወኑበት ጠቁመዋል።
በዚህ እርከን የሚመጡ ተሳታፊዎች በምክክርና በውይይት የአጀንዳ ሀሳቦች የሚያመጡ ሲሆን ሀሳቦችን የጋራ በማድረግ ያሰባስባሉ ያደራጃሉ ብለዋል።
በመጨረሻም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮቻቸውን እንደሚመርጡ ገልጸዋል።
በቀጣይም ኮሚሽኑ ተመሳሳይ መርሀ ግብሮችን በክልሎች እና ከተማ አስተዳደር እንደሚያከናውን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያውያን የምክክሩን ፋይዳ በመረዳት ዝግጅት እንዲያደርጉና በዚህ ምክክር በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በምክክሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራትና ተቋማት፣ የመንግስት አካላት፣ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች የሚመካከሩበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የአጀንዳ ግብአታቸውን የሚያዘጋጁበት እና በሀገራዊ ጉባኤ የሚወክሏቸውን ተሳታፊዎች የሚመርጡበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የኃሳብ ልዩነትና አለመግባባት በአካታች አገራዊ ምክክር ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ይታወቃል።