ዩኒየኑ የግብርና ምርቶችን ለአባላቱና ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በማቅረብ ገበያን እያረጋጋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒየኑ የግብርና ምርቶችን ለአባላቱና ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በማቅረብ ገበያን እያረጋጋ ነው
ደብረ ብርሃን ፤ ግንቦት 18/2016 (ኢዜአ)፦ በሰሜን ሽዋ ዞን የሚገኘው የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለአባላቱና ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በማቅረብ የገበያ ዋጋ ማረጋጋት ስራ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒየኑ 19ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በደብረ ብርሀን ከተማ ዛሬ አካሄዷል።
ለአባላቱም ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ የትርፍ ክፍፍል ማድረጉንም ገልጿል።
የዩኒየኑ ስራ አስኪያጅ አቶ አስገልለው ሙሉ ሸዋ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ዩኒየኑ የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለአባላቱና ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ተግባሩን እየተወጣ ነው።
የአባላቱን ጥቅም ለማስከበርም ዩኒየኑ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ከ2013 አስከ 2015 ዓ/ም ባሉት ዓመታትም ዩኒየኑ ባካሄደው የሰብል፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና የግብርና ግብዓት ግብይት ከ114 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ብር ጠቅላላ ትርፍ ማግኘቱን ተናግረዋል።
ከዚሁ ትርፍ ውስጥም ከ57 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ለአባላት የትርፍ ክፍፍል ማድረጉንም አስታውቀዋል።
የትርፍ ክፍፍሉም እንደ ግብይት እንቅስቃሴያቸው የሚወሰን ቢሆንም በህብረት ስራ ማህበር ደረጃ ከፍተኛ ትርፍ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል።
የዩኒየኑ ጠቅላላ ካፒታልም አሁን ላይ 238 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር መድረሱን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የገበያ ማረጋጋት ስራውን በማጠናከር የአባላቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ህብረት ስራ ማህበራት ማደራጃ ተጠሪ ጽህፈት ቤት የማደራጃ ቡድን መሪ አቶ ጌዲዮን ተስፋይ በበኩላቸው፤ ህብረት ስራ ማህበራቱ በተናጠል ሊፈቱ የማይችሉ ችግሮችን በጋራ በመፍታት የተሻለ ስራ እየሰሩ ነው።
ህብረት ስራ ማህበራት የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን ለአባላቱና ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ከፍተኛ ሚና እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
በማህበራቱ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድና የተሻለ የግብይት እንቅስቃሴ እንዲያከናውኑ ለማስቻልም በአዲስ የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በሞረትና ጅሩ ወረዳ የገርባ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ድንቁ በበኩላቸው፤ ተደራጅቶ መስራት ለአውቀትና ልምድ ሽግግርም ሆነ ለሃብት ግኝት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።
ማህበሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት 21 ሺህ 608 ኩንታል የተለያዩ ሰብሎችን ከአባላቱ በመግዛት እና የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በመሸጥ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ተናግረዋል።
በቀጣይ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአባላት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የአባላቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃማነትን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
ማህበሩ ባደረገው የግብይት እንቅስቃሴ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ መገኘቱን የገለፁት ደግሞ የዲላሞ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ቃኘው ድንቁ ናቸው።
የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን 142 መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራትና 154 ሺህ አባላት እንዳሉትም ለማወቅ ተችሏል።